በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የናይጄሪያን የምርጫ ውጤት የሚቃወሙ ሰልፎች ቀጥለዋል


ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች
ለተቃውሞ የወጡ ሰልፈኞች

በናይጄሪያ የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽንና መንግሥት፣ ከሳምንታት በፊት ተደርገው የነበሩ የፕሬዝዳንታዊ እና የአገረ ገዢዎች ምርጫ ውጤቶችን ዳግም እንዲመረምሩ ግፊት ለማድረግ የተቃውሞ ሰልፍ በማካሔድ ላይ ናቸው፡፡

በኹለቱም ምርጫዎች ወቅት፥ ሞትን ያስከተሉ ጥቃቶች፣ የአካል ጉዳት፣ ድምፅ ሰጪዎችን ማሸማቀቅ እና ድምፅ እንዳይሰጡ ዕንቅፋት መፍጠርን የመሰሉ ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

ከ700 በላይ የሚኾኑ ሰዎች ምርጫውን አውከዋል፤ በሚል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና በአገሪቱ ሕግ መሠረት ለፍርድ እንደሚቀርቡ ፖሊስ ባለፈው ሰኞ አስታውቋል፡፡

“የነናይጄሪያ እንቅስቃሴ” የተሰኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድን፣ ትላንት ማክሰኞ ሰልፍ ማድረጉ ሲታወቅ፤ ባለፈው ሳምንት የተጀመረውና በየዕለቱ እየተደረገ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች፣ የምርጫ አፈጻጸሙን በተመለከተ ተፈጥሯል ላሉት ችግር ሓላፊነት እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ በምርጫው ቴክኒካዊ ችግር ከማጋጠሙም ባሻገር፣ በብዙ ቦታዎች ሁከት፣ ድምፅ ሰጪዎችን ማሸማቀቅ እና ድምፅ እንዳይሰጡ ዕንቅፋት መፍጠርን የመሰሉ ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

“ችግሮች መኖራቸው እየታወቀ፣ የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን በጥድፊያ ዐውጇል፡፡በተጨማሪም ኮሚሽኑ፣ የምርጫ ውጤቶችን ከየአካባቢው በኢንተርኔት እንደሚያስተላልፍ የገባውን ቃሉን አልጠበቀም፤” ሲሉ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

ቴክኒክንና ጸጥታን በተመለከተ ለተፈጠሩት ችግሮች፣ መጸጸቱንና ወደፊት እንደሚያሻሻል፣ የምርጫ ኮሚሽኑ በዚኽ ወር መጀመሪያ ላይ አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሰቦች ላይ፣ 66 የሚኾኑ የጦር መሣሪያዎች መያዙን፣ ፖሊስ አክሎ አስታውቋል፡፡

700 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ 66 የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኑ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ በናይጄሪያ ምርጫ ወቅት በርካቶችን ድምፅ ከመስጠት ያገደውን ሁከት አውግዞ፣ ባለሥልጣናት ጥፋተኞችን እንዲቀጡ ባለፈው ሳምንት ጥሪ አድርጓል፡፡

ኹለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የምርጫውን ውጤት በፍርድ ቤት ለመሞገት ክሣቸውን ያስገቡ ሲኾን፣ ፕሬዝዳንት ኾነው የተመረጡት ቦላ አሕመድ ቲኑቡ፣ ከኹለት ወራት በኋላ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ፤ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተቃውሞ ሰልፎቹ ወይም የፍርድ ቤቱ ሒደት፣ አወዛጋቢውን የምርጫ ውጤት ይቀይሩ እንደሁ ለማየት በርካቶች ይጠባበቃሉ፡፡

XS
SM
MD
LG