በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ የተስተጓጎለው ምርጫ እንዲካሔድ ጠየቁ


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ የተስተጓጎለው ምርጫ እንዲካሔድ ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:22 0:00

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ስድሰተኛው አገራዊ ምርጫ ባልተካሔደባቸው የክልሉ አካባቢዎች ምርጫ እንዲካሔድ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠየቀ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ እና የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ሊቀ መንበር አቶ አብዱልሰላም ሸንግል፣ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሰባት ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ውይይት ከአደረጉ በኋላ፣ በክልሉ ምርጫ እንዲያካሒድ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን መጠየቃቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ሰብሳቢው፥ ክልሉ እየተመራ ያለው፣ በ2007 ዓ.ም. በተካሔደው አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ በተመረጠው ምክር ቤት መኾኑን መገምገማቸውን ጠቅሰው፣ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ፣ የምርጫ ቦርድ ዝግጅት አድርጎ ምርጫውን እንዲያስፈጽም መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ከዚኽ ውሳኔ ላይ የደረሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ ብልጽግና፣ ጉሕዴን፣ ቤሕነን፣ አብን፣ ቦዴፓ፣ ኢዜማ እና መኢአድ እንደኾኑ ሰብሳቢው ዘርዝረዋል፡፡ የፓርቲዎቹ እጩ ተወዳዳሪዎች የተመዘገቡት፣ ከኹለት ዓመት በፊት በመኾኑ፣ በዐዲስ መልክ እንዲመዘገቡ መጠየቃቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አብዱልሰላም፣ “ከዚኽ በፊት የተሠራጩ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶችም ተቃጥለው፣ በዐዲስ መልክ እንዲሰራጩ ጠይቀናል፤” ብለዋል።

ይህን የጠየቁበት ምክንያት፥ የሞቱ፣ ወደ ሌላ ቦታ የሔዱ እንዲሁም፣ እጩ ያላቀረቡ ፓርቲዎች በመኖራቸው ነው፤ ሲሉ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡

በሰኔ ወር 2013 የተካሔደው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በክልሉ የመተከል እና የካማሺ ዞኖች

አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይ ሳይካሔድ መቅረቱን ያወሱት አቶ አብዱልሰላም፣ በ2013 ዓ.ም. የታተሙ ምርጫ ነክ ሰነዶች እንዲወገዱ እና የመራጮች ምዝገባ በዐዲስ መልክ እንዲካሔድ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) የፖለቲካ ጉዳዮች ሓላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ በበኩላቸው፣ የክልሉ ጸጥታ በከፍተኛ ኹኔታ መሻሻሉ፤ ምርጫ ለማካሔድ አንድ አስቻይ ኹኔታ መኾኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ መንግሥት በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ አካላት ጋራ የሰላም ስምምነት ተፈራርሞ፣ ሰላም እና መረጋጋቱ እየሰፈነ በመምጣቱ ምርጫ እንዲካሔድ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ታደሰ ለማ፣ በጋራ ምክር ቤቱ ወደ ጽ/ቤታቸው የቀረበ ጥያቄ አለመኖሩን ገልጸዋል። ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል የምርጫ ሰሌዳ የሚያወጣው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደኾነ በማስታወስ፣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ተግባር ያን ማስተባበር እንደኾነ አስገንዝበዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ “በክልሉ ምርጫ ለማስፈጸም የወጣ የጊዜ ሰሌዳ የለም፤” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ጥያቄውን እንደተቀበለው ጠቅሶ፣ በሒደት ምላሽ እንደሚሰጥበት አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG