በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናም ያገኛሉ” - ሚቲኦሮሎጂ


“በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናም ያገኛሉ” - ሚቲኦሮሎጂ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:07 0:00

ድርቅ ሲመላለስባቸው የነበሩት፣ የደቡብ እና ደቡባዊ ምሥራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ አሁንም ከመደበኛ በላይ ዝናም እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጠቆመ።

አቶ ሙሉዓለም አበራ፣ በኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኢንስቲትዩት የረዥም ጊዜ ትንበያ እና የድርቅ ክትትል ዴስክ ሓላፊ በተለይ የቦረና፣ የጉጂ፣ የባሌ እና ደቡባዊ የሶማሌ ክልል አካባቢዎች፣ በመጠኑ ከመደበኛ ከፍ ያለ ዝናም እንደሚያገኙ ጠቁመዋል። የቦረና ዞን ነዋሪዎች በዝናሙ ቢደሰቱም፣ አሁንም በድርቅ የተጎዱ ከብቶቻቸውን በዝናሙ እንዳያጡ ስጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

አቶ ሙሉዓለም አበራ፣በደቡብ ኦሮሚያ፣ በቦረና፣ በጉጂ፣ በደቡባዊ የባሌ ዞን አካባቢ እንዲሁም፣ በድርቅ በተጎዱ ዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ፣ በመጠኑ ከፍ ያለ ዝናም እንደሚጠብቅ ተናግረዋል፡፡

“ለምሳሌ፤ ሞያሌን ብንወስድ፥ በማርች 22 ቀን፣ 88 ሚሊ ሊትር ተመዝግቧል። ይህም እጅግ በጣም ከባድ ዝናም ነው። ስለዚህ፣ እነዚህ አካባቢዎች፣ በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት፣ ከ30 ሚሊ ሊትር ዝናም በላይ ያገኛሉ።” ያሉት አቶ ሙሉዓለም “በደቡባዊ ሶማሌ ክልል፣ ቀብሪደኀርን ጨምሮ፣ በቀን ከ30 እስከ 100 ሚሊ ሊትር ዝናም ሲጥል ነበር። አሁንም ከሕንድ እና የአረብ አገሮች አካባቢ እየገባ ያለው ርጥበት አዘል አየር፣ ለከባድ ዝናም አስቻይ ኹኔታዎችን እየፈጠረ ስለኾነ፣ ርጥበቱም እየቀጠለ ነው የሚመጣው፡፡” ብለዋል።

ቦረና ዞን፣ ዝናም ከጣለባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ የያቤሎ ከተማ ነዋሪ አቶ ጎልቻ ዶዮ፣ በዞኑ በሚገኙ በኹሉም ወረዳዎች ለማለት በሚቻል ኹኔታ ዝናሙ መጣሉን ተናግረው፣ “ነገር ግን ያልተዳረሰባቸው የገጠር ቀበሌዎችም አሉ፤” ብለዋል።

“ዝናም ዘንሟል ማለት ሕዝቡ ከችግር ወጥቷል ማለት አይደለም፤ ሕዝቡ አሁንም አሳሳቢ ጉዳዮች አሉበት፡፡ ከአሁን በኋላም ዝናሙ በዚኹ አዝማሚያው ከቀጠለ፣ የሚሞቱ ከብቶች ይኖራሉ። ሌሊቱን ዘንሞ ካደረ፣ ብዙ ከብቶች ከተኙበት ላይነሡ(ላይቋቋሙት) ይችላሉ - ከቅዝቃዜው አንጻር። ሣርም ቢኾን ለመብቀል፣ ከኹለት ሳምንት በላይ ሊያስጠብቅ ስለሚችል፣ አሁንም ፍራቻ አለን።”

የቦረና ዞን ነዋሪው አቶ ጎልቻ፣ አሁንም በዞኑ በድርቅ ለተጎዱ ነዋሪዎች የሚደረግ ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት አመልክተው፣ ዘር መዝራት ለሚሹ አርሶ አደሮች፣ ከብቶቻቸው ስለሞቱባቸው ድጋፍ እንደሚሹ አስታውቀዋል።

አቶ ሙሉዓለም አበራ፣ በኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኢንስቲትዩት የረዥም ጊዜ ትንበያ እና የድርቅ ክትትል ዴስክ ሓላፊ፣ በአሁኑ ወቅት ቦረናን ጨምሮ በደቡብ እና በደቡባዊ ምሥራቅ አካባቢዎች እየጣለ ያለው የበልግ ዝናም ዋነኛ የአካባቢው የዝናም ወቅት መኾኑን አስታውሰው፣ “ከዝናሙ የሚገኘውን ውኃ በማቆር ለልዩ ልዩ ጥቅሞች መዋል አለበት፤” በማለት መክረዋል። የዝናሙን ቀጣይነት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ሚቲኦሮሎጂ ኢንስቱትዩት፣ በቅርቡ የትንበያ ጥናት ይፋ እንደሚያደርግ አቶ ሙሉዓለም ጠቁመዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ዘገባ ያገኛሉ።

XS
SM
MD
LG