በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሕይወቱን ለብዙኀ ሕይወት የሰጠ ዐቃቤ ፍጥረት


ሕይወቱን ለብዙኀ ሕይወት የሰጠ ዐቃቤ ፍጥረት
please wait

No media source currently available

0:00 0:18:49 0:00

“ተወልደ ደስ የሚያሰኝ ምዑዝ አባት ነበር፡፡ የመልካም አባቶች ኹሉ ምሳሌ ነው፤” ይላሉ ዶር. ሳራ፤ ስለ ሳይንቲስቱ አባታቸው ሲናገሩ፡፡ “ከእናቴ ጋራ የዕፀዋትን ናሙና ሊሰበስቡ ሲወጡ፣ ይዘውን ይዞራሉ፡፡ ዕፀዋት ለመሰብሰብ ተራራ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ፡፡ እኔ ደግሞ ይደክመኝና እሽኮኮ አድርገኝ እለዋለኹ፤ በትከሻው ተሸክሞኝ ነበር የሚዞረው፤” በማለት ያወሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከአፈራቻቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ የኾኑት ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር(ዶር.) ፥ በብዙኀ ሕይወት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ ብዙ ምርምሮችን ሠርተዋል፡፡

ተወልደ(ዶር.)፣ ከተፈጥሮ ጋራ የነበራቸው ፍቅር፣ ከልጅነታቸው የጀመረ እንደኾነ ዶ/ር ሳራ ገልጸዋል፡፡ በአንድ ወቅት አባታቸው ወደተወለዱበት አካባቢ ሔደው ስለ እርሳቸው የሰሙትን እንዲህ ይገልጻሉ፤ “ከልጅነቱ ጀምሮ ይኸኛው ቅጠል ከዚያኛው ቅጠል ይለያል፤ እያለ ያስተውላል፤ ይመረምራል፡፡ ነገሮች እንዴት እንደሚሠሩ እና እንዴት እንደሚኖሩ ለማወቅ ይጓጓ ነበር፡፡ ዕፀዋት እና ተፈጥሯቸው ያስደስተው እንደነበር የአካባቢው ሰዎች ነግረውኛል፡፡”

ዓድዋ አካባቢ በምትገኝ ርባገረድ በምትባል መንደር የተወለዱት ተወልደ ብርሀን(ዶር.)፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንግሥተ ሳባ፣ የኹለተኛ ደረጃን ደግሞ በዊንጌት ት/ቤት ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው በከፍተኛ ነጥብ ተመርቀዋል፡፡ ወዲያውኑ፣ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን፣ “የምድራችን ጀግና” በሚል ርእስ የሕይወት ታሪካቸውን የሰነደው ዘነበ ወላ ጽፏል፡፡

ዘነበ በመጽሐፉ ስለ ተወልደ ብርሃን(ዶር.) የድኅረ ምረቃ ትምህርት ዕድል የሚከተለውን አስፍሯል፤ “ወደ እንግሊዝ ሔዶ እንዲማር የትምህርት ዕድል ሲሰጠው፣ እርሱ ግን ቤተሰቦቼ ድኾች ናቸው፤ ወላጆቼን የምደጉመው እኔ ነኝ፤ ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት ቤተሰቦቼን የማግዝበት መንገድ ስለሌለኝ አልሔድም፤” አላቸው፡፡ ይህን ጊዜ ዩኒቨርሲቲው፣ በየወሩ 100 ብር ለወላጆቹ እንደሚሰጣቸው ነግሮት፣ ሔደኽ ተማር፤ አለው፡፡ ተወልደም በዚኽ ተስማምቶ ወደ ኖርዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ አምርቶ ትምህርቱን ጀመረ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ውጤቱን አይቶ፣ በቀጥታ የዶክትሬት ዲግሪ መጀመር ትችላለኽ፤ አለው፡፡ ኹለተኛ ዲግሪ አልሠራም፡፡ የዶክትሬት ዲግሪውን በሥነ ምኅዳር ላይ ሠርቶ፣ በ1960 ወደ ሀገሩ ተመልሶ፣ በዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመረ፤” ብሏል፡፡

ተወልደ ብርሃን(ዶር.)፣ በመምህርነት በሠሩባቸው ጊዜያት፣ ለበርካቶች አርኣያ እንደኾኑ፣ ከተማሪዎቻቸው አንዱ የነበሩት ፕሮፌሰር እንደሻው በቀለ ይናገራሉ፡፡ “እርሱን መግለጽ ቀላል አይኾንም፤ በቸገረን ጊዜ በቤቱ ተቀምጠን የኖርን ልጆቹ ነን፤” በማለት ሰብአዊነታቸውን አዘክረዋል፡፡

ተወልደ ብርሃን(ዶር.) ከእንግሊዝ ሀገር በመጡበት በ1961፣ ፕሮፌሰሩ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበሩበት የዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዳገኟቸው ያስታውሳሉ፡፡ “እንደ ምሳሌ የምናየው ሰው ነበር፤ እርሱ አቅጣጫ ያሳየንና መስመር ያስያዘን፣ አርኣያም የኾነን መምህራችን ነው፡፡ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ አሻራ አኑሯል፤ በእኔ ሕይወት ደግሞ የተለየ ቦታ አለው፡፡ በተገፋኹበት፣ በተበደልኹበት፣ ሰው አጥቼ ሰው በምፈልግበት ወቅት ያገኘኹት ሰው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ኹኔታ ምክንያት እዚኽ መኖር ስላልቻልኹ፣ የዶክትሬት ዲግሪዬን ይዤ ወደ አሥመራ የሔድኹት ተወልደ እዚያ ስለነበረ ነው፡፡ እንደ ልጆቹ እየተከባከበ አኑሮኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስን በኋላም እስከ ዕለተ ኅልፈቱ ድረስ እንጠያየቅ ነበር፡፡ ከልጆቹ ቀጥዬ ራሴን እንደ ልጁ የምቆጠር ሰው ነኝ፡፡ ከተወልደ ጋራ በዘመኑ አነጋገር በብሔር አንገናኝም፤ እኔ ከአርሲ እርሱ ደግሞ ከትግራይ ኾነን፣ በሰውነት የተገናኘን ሰዎች ነን፤” ብለዋል ፕሮፌሰር እንደሻው፡፡

/ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ/

XS
SM
MD
LG