በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን የእስር ማዘዣ ወጣባቸው


 ፎቶ ፋይል ፡ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ጥቅምት 2014 ዓ.ም ከሞስኮ ወጣ ብላ በምትገኘው ኖቫ ኦጋራዮ በተባለች ቦታ ሲናገሩ
ፎቶ ፋይል ፡ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ጥቅምት 2014 ዓ.ም ከሞስኮ ወጣ ብላ በምትገኘው ኖቫ ኦጋራዮ በተባለች ቦታ ሲናገሩ

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ) በሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ፡፡ ፍርድ ቤቱ ማዘዣውን ያወጣው ህፃናትን ከዩክሬን ማፈናቀልን ጨምሮ በጦር ወንጀሎች ተጠያቂ በመሆናቸው ነው ብሏል።

ፑቲን ህፃናትን በሕገ ወጥ መንገድ በማፈናቀልና በኃይል ከተያዙ የዩክሬን አካባቢዎች ሕፃናትን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሩሲያ በማዘዋወር ወንጀል ተጠርጣሪ ናቸው ብሏል። ድርጊቱ የተፈፀመው ከየካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ ሩሲያ በኃይል በያዘቻቸው የዩክሬናዊያን ግዛት ውስጥ የተፈጸሙ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

“ፑቲን ወንጀሉን በቀጥታ በግላቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር በማበር እንደፈጸሙት የሚያሳይ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ” ሲል ፍርድ ቤቱ በማዘዣው አስታውቋል።

ፍርዱ ቤቱ ተፈፅሟል ባለው የወንጀል ድርጊት ከፑቲን በተጨማሪ የሩሲያ የህፃናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ሎቮቫ-ቤሎቫም ተፈላጊ አድርጓል።

ፑቲን የወንጀል ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉትን የሲቪልና ወታደራዊ የበታች ባለሥልጣኖቻቸውን በአግባቡ መቆጣጠር ባለመቻል ወይም ደግሞ ባለሥልጣናቱ ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ሆን ብሎ በመተው ተጠያቂ ተደርገዋል።

የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ) ፕሬዚዳንት ፒዮትር ሆፍማንስኪ ማዘዣውን በተመለከተ በሰጡት በቪዲዮ የታገዘ መግለጫ ፤ ፍርድ ቤቱ የዳኞቹን ትእዛዝ የሚያስፈፅምበት የራሱ የፖሊስ ኃይል እንደሌለው ገልፀው "ትእዛዙን ማስፈፀም የሚችለው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ነው" ብለዋል።

"አይ.ሲ.ሲ እንደ ፍድር ቤትነቱ የበኩሉን እየሠራ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ "ዳኞቹ የእስር ማዘዣ አውጥተዋል፣ አፈፃፀሙ የሚወሰነው ግን በዓለም አቀፍ ትብብር ነው።" ብለዋል።

ሩሲያ የፍርድ ቤቱን ውንጀላና ማዘዣ "ባዶ እና ዋጋ ቢስ ነው" በማለት ውድቅ አድርጋዋለች፡፡የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ፤ ለማዘዣው በሰጡት ምላሽ " የሕግ አኳያን ጨምሮ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ለሀገራችን ምንም ትርጉም የላቸውም" ብለዋል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ የፍትህ ተባባሪ ዳይሬክተር ባልኪስ ጃራህ “አይሲሲ ፑቲንን በተፈላጊ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የከተታቸው ሲሆን ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ወረራ ወንጀሎችን ለረጅም ጊዜ ያበረታታውን ያለመክሰሰ መብት ለማስቆም የመጀመሪያውን እምርጃ ወስዷል” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG