በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ለሶማሊያ የምሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ እየጨመረች ነው


ፎቶ ፋይል፦ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ
ፎቶ ፋይል፦ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ

“በዓለም ትልቁ እና አደገኛው የአል-ቃይዳ መረብ” ብላ አሜሪካ በምትገልጸው ቡድን ላይ ሶማሊያ ድል እያገኘች መሆኑን በመገንዘብ፣ ወታደራዊ ዕርዳታዋን እየጨመረች መሆኑን ከአሶስዬትድ ፕረስ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

ትናንት ማክሰኞ 61 ቶን የሚመዝን መሳሪያ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሹ መድረሱን ሪፖርቱ አመልክቶ ይህም በሶማሊያ መሪነት በአል-ሻባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ለማጠናከር ነው ብሏል፡፡

ከቃጣር፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምትስ እንዲሁም እንግሊዝ ጋር በመሆን ባወጣቸው መግለጫ፣ ሶማሊያ መሣሪያዎችን በራሷ ለማስተዳደር እንድትበቃና ተመድ የጣለባት የመሣሪያ ግዢ ማዕቀብ እንዲነሳላት አሜሪካ ጥረት እነደምታደርግ አስታውቃለች፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት በርካታ ቦታዎችን በተቆጣጠረውና እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት በሚጥረው አል-ሻባብ ላይ አጠቃላይ ጦርነት ያወጀው የፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ መንግሥት ባለፉት ወራት በርካታ ቦታዎችን አስለቅቋል፡፡

አሜሪካ 450 የሚሆኑ ወታደሮች በሶማሊያ አሏት፡፡ ይህም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የአሜሪካን ጦር ለማሰወጣት የውሰኑትን ውሳኔ የወቀቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቀልብሰው ጦሩ ቆይታውን እንዲቀጥል በመወሰናቸው ነው፡፡

አሜሪካ የሶማሊያን ጦርና የአፍሪካ ኅብረትን ልዑክ ጦር በድሮን ጥቃት፣ በመረጃና በሥልጠና ትረዳለች፡፡

የአፍሪካ ኅብረትን ልዑክ ጦር በመጪው የፈረንጆች ዓመት 2024 መጨረሻ ላይ የጸጥታ ኃላፊነቱን ለሶማሊያ ጦር አስረክቦ እንደሚለቅ ይጠበቃል፡፡

XS
SM
MD
LG