የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ ቡካሬስት -9 ተብሎ የሚጠራው ስብስብ አባል ሀገሮች መሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተዋል፡፡
በአህጽሮት ቢ - 9 ተብለው የሚታወቁት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ምስራቃዊ ክፍል አባል ሀገሮች ቡልጌሪያ፡ ቼክ ሪፐብሊክ፡ ኤስቶኒያ፡ ሀንጋሪ፡ ሊቱዌኒያ፡ ላትቪያ፡ ፖላንድ፡ ሮሜኒያ እና ስሎቫኪያ ናቸው፡፡
እምብዛም የማይታውቀውን ይህንን ስብስብ እ.አ.አ በ2015 ዓመተ ምህረት ያቋቋሙት የሮሜኒያ ፕሬዚደንት ክላውስ ኢዮሀኒስ እና የፖላንድ ፕሬዚደንት አንድሬ ዱዳ ናቸው፡፡ ስብስቡን የመሰረቱበት ምክንያትም አዲሶቹ የህብረቱ አባል ሀገሮች የድርጅቱን የባልቲክ እና ጥቁር ባህር አካባቢን ጸጥታ እና መረጋጋት የማሻሻል ግብ በህብረት ለመደገፍ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በሞስኮ ተጽዕኖ ስር ለነበሩት እና አሁን ደግሞ የሞስኮን ተስፋፊነት በስጋት ለሚመለክቱት ለአዲሶቹ የህብረቱ አባላት ጸጥታ እንደምትቆም ፕሬዚደንት ባይደን በድጋሚ አረጋግጠውላቸዋል፡፡
የቢ-9 አባል ሀገሮች የትናንቱን ስብሰባቸውን ያካሄዱት ሞስኮ በዩክሬይን እና በሮሜኒያ መካከል የምትገኘውን ትንሿን በኔቶ ያልታቀፈች ሀገር የሞልዶቫን ጸጥታ ለማናጋት የምትፈጽመው ተግባር እያሳሰበ ባለበት በዚህ ወቅት ነው፡፡
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ በበኩላቸው የሩስያ ፕሬዚደንት ፑቲን ለሰላም ሳይሆን ለተጨማሪ ጦርነት እየተዘጋጁ ናቸው በማለት አስተጋብተዋል፡፡
የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን እ.አ.አ የሞልዶቫን ሉዐላዊነት ለማክበር ያወጡትን አዋጅ ባለፈው ማክሰኞ እንደሰረዙት ይታወሳል፡፡ የፑቲን ዕርምጃ በሞልዶቫ ዋና ከተማ ቺሲናዉ ያለውን ስጋት አባብሶታል፡፡ የሞልዶቫ ጠቅላይ ሚንስትር ናታሊያ ጋቭሪሊታ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም “ሩስያ በፕሮፓጋንዳ፡ በሀሰተኛ መረጃ እና በተደጋጋሚ የኢንተርኔት ጥቃት በማካሄድ መፈንቅለ መንግሥት ሴራ እየፈጸመችብን ነው” ሲሉ ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ማይያ ሳንዱ አስጠንቅቀዋል፡፡
ባይደን ማክሰኞ ዕለት ዋርሳው ላይ ላነጋግሯቸው የሞልዶቫ ፕሬዚደንት የዩናይትድ ስቴትስን ድጋፍ ያረጋገጡላቸው መሆኑን ኋይት ሀውስ አመልክቷል፡፡
የቢ 9 ስብስብ አባል ሀገሮች ከሀንጋሪ እና ከቡልጌሪያ በስተቀር ለዩክሬን ወታደራዊ ዕርዳታ እንዲሰጣት አጥብቀው ከሚደግፉ ሀገሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡