በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓረብ ሃገራት መሪዎች የእስራኤል ድርጊት የቀጠናውን ሰላም ያናጋል ሲሉ አስጠነቀቁ 


የአረብ ሃገራት መሪዎች በካይሮ
የአረብ ሃገራት መሪዎች በካይሮ

ከአስር በላይ የሚሆኑ የዓረብ እና የእስላማዊ ሃገራት ከፍተኛ መሪዎች እስራኤል ከፍልስጤም ጋር የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፤ በእየሩሳሌም እና በዌስት ባንክ እየፈጸመችው ያለው ድርጊት የቀጠናውን ስጋት የሚያባብስ ነው ሲሉ አስጠነቀቁ።

በዛሬው ዕለት በካይሮ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የግብጹ ፕሬዘዳንት አብደል ፈታ አልሲሲ፣ የጆርዳኑ ንጉስ አቡድላህ ሁለተኛ እና የፍልስጤሙ ፕሬዘዳንት ማህሙድ አባስ ከሌሎች አያሌ ከፍተኛ ሹማምንት እና የውጭ ጉዳይ ሚስትሮች ጋር ተሰብሰበዋል።

ይህ ከፍተኛ የመሪዎች ስብሰባ በእየሩሳሌም እና እስራኤል በተቆጣጠረቻቸው በጎረቤት ግዛቶች ላይ በዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ግጭት እየተካሄደ ባለበት ሰዓት የተደረገ ነው። እስራኤል የጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 45 ፍልስጤማዊያንን የገደለች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ከእስራኤል ወገን የሞቱት አስር ብቻ መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ አረጋግጫለሁ ብሏል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች የእስራኤል በዌስት ባንክ እና በእየሩሳሌም ቤት ማፍረስ አና ሰዎችን የማስፈር ዘመቻን ጨምሮ እየወሰደችው ነው ያሉትን የተናጥል እርምጃ አውግዘዋል።

ተሳታፊዎቹ የእስራኤል ባለስልጣናት የእስራኤል እና የፍልስጤም የውዝግብ ማዕከል የሆነውን እና በሙስሊም ሆነ በአይሁዶች ዘንድ ቅዱስ የሆነውን አካባቢ መጎብኘታቸውንም አውግዘዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ከእስራኤል መንግስት የተሰጠ ምላሽ የለም።

XS
SM
MD
LG