በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በፓኪስታን ሃይማኖትን አንቋሿል የተባለ ወጣት ተገደለ


ፎቶ ፋይል (ቪኦኤ)
ፎቶ ፋይል (ቪኦኤ)

በፓኪስታን ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽ ንግግር አድርጓል የተባለና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረን ተጠርጣሪ በቁጣ የተሰባሰቡ ሰዎች ከፖሊስ ነጥቀው ገድለዋል።

ሞሃመድ ዋሪስ የተባለው ወጣት እስልምናንና ቁራንን ተሳድቧል በሚል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበረ ቢሆንም፣ የተቆጡ የሃይማኖቱ ተከታዮች ፖሊስ ጣቢያውን በመውረርና ፖሊሶቹን በማባረር ግለሰቡን ቀጥቅጠው ገድለዋል።

በአብዛኛው የእስልምና ተከታዮች በሚገኙባት ፐንጃብ አውራጃ ያሉ የፖሊስ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት ፖሊስ ተጨማሪ ሃይል በማሰባሰብ የግለሰቡን አስከሬን ከመቃጠል አድኗል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመላለሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እርቃን የሆነው የግለሰቡ በድን በመንገድ ላይ ሲጎተት አሳይተዋል።

በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሉባት በፓኪስታን ሃይማኖትን ማንቋሸሽ በሞት የሚያስቀጣ ድርጊት ቢሆንም፣ ሃይማኖትን ሰድቧል የተባለን ሰው በጥርጣሬ ብቻ በቁጣ የተሰባሰቡ ሰዎች መግደል እየተለመደ መጥቷል።

ከሁለት ዓመት በፊት እንድ ስሪላንካዊ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሃይማኖትን አንቋሸሃል በሚል የሃሰት ውንጀላ በሰራተኞቹ ተደብድቡ ተገድሏል፡

በኋላ በተደረገው ማጣራት ግለሰቡ ድርጊቱን ባለፈጸሙ በግድያው የተሳተፉ ስድስት ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ወስኗል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነጻነት ኮንሚሽን የተባለው ተቋም ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ ሃይማኖትን ማንቋሸሽ የተመለከተው ህግ በፓኪስታን አክራሪ የእስልምና ተከታዮች የሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን ለማጥቃት እንደምክንያት እየተጠቀሙበት ነው።

XS
SM
MD
LG