በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኦሮምያ ክልል ሰላም ድርድር እንዲጀመር ተጠየቀ


ኦሮምያ ክልል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ሰላማዊ መፍትኄ እንዲያገኝ የሚጠይቅ ግልፅ ደብዳቤ በውጭ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ማኅበረሰቦችና ሲቪል ማኅበራት ጠይቀዋል።

የኦሮሞ ውርስና ተሟጋች ማኅበር እየተባለ የሚጠራው ቡድን ትናንት /ሐሙስ/ ይፋ ባደረገውና ለዝግጅት ክፍላችን በላከው ግልፅ ደብዳቤ ማኅበረሰቦቹና እራሱም የሚገኝበት ሲቪል ማኅበራት ደብዳቤያቸውን ይድረስ ያሉት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ለኦሮምያ ፕሬዚዳንት ሺመልስ አብዲሳና የኦነግ-ኦላ ወይም /የኦሮሞ ነፃነት ጦር/ ዋና አዛዥ ላሏቸው ኩምሳ ድርባ ወይም ጃል ማሮ ነው።

“ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሺሆች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ሲቪሎች ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ የስቃይ አያያዝ ተፈፅሞችባቸዋል፣ ሚሊዮኖች ደግሞ ተፈናቅለዋል” የሚለው ይህ መግለጫ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስትያን ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት ይህንን አደገኛ ያለውን ሁኔታ አባብሶታል ብሎ እንደሚሰጋ ደብዳቤው ይናገራል።

የኦሮሞ ህዝብ የሁከት አዙሪት ተጋርጦበታል ባለው በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወደ ድርድር ጠረጴዛ መቅረብ አለባቸው ብለው የኦሮሞ ዳያስፖራ ማኅበረሰቦች እንደሚያምኑ የሚጠቁመው ግልፅ ደብዳቤ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትኄ እንዲፈልጉ አሳስቧል።

የሰላም ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ቢመራ የተሳካ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ደብዳቤው አመልክቶ ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብም ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቋል።

በደብዳቤው ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትን፣ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥትን፣ የኦሮሞ ነፃነት ጦርንና ለሌሎችም በደብዳቤው ውስጥ የተጠቀሱ ወገኖችን ሃሳቦችና አስተያየቶች ለማግኘት እየሠራን ነው።

XS
SM
MD
LG