በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ግድያ ተፈጽሟል” ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች


ሻሸመኔ ከተማ /ፎቶ ፋይል
ሻሸመኔ ከተማ /ፎቶ ፋይል

በሻሸመኔ ከተማ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ግድያ መፈፀሙን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች። በቤተክርስቲያን ስለቀረበው ክስና በሻሸመኔ ስለተፈጠረው ጉዳይ እስካሁን ከመንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም። የቤተክርስቲያን ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ፣ "የካቲት 5/2015 ዓ.ም 'በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ካሕናትና ምዕመናን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ'' ሲል ሲኖዶስ አውጇል።

ሲኖዶሱ ዛሬ ጥር 27/2015 ዓ.ም አመሻሹን በሰጠው መግለጫ፤ በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ “ሕገ ወጦቹ” ሲል የጠቀሳቸው አካላት “በደብረ ስብሃት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን በሕገ መልኩ ወረራ ለመፈፀም ባደረጉት እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያንን ለመጠበቅ በወጡ ምዕመናን ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ በአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈፅሟል” ብሏል።


ምን ያህል ሰው እንደተገደለ ያልገለፀው ሲኖዱሱ፤ ሌሎች በቁጥር ያልታወቁ ሰዎችም ከፍተኛና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል። ለአሜሪካ ድምጽ አስተያየታቸውን የሰጡ እና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች፣ ቤተክርስቲያን ባለበት አካባቢ በርካታ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል እና የከተማው ፖሊሶች እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ የተኩስ ድምጾች እንደሚሰሙም ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ድምጽ ስለጉዳዩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡
በከተማዋ ስለተከሰተው ችግር እና ስለደረሰው ጉዳት ከመንግሥት ወገን ግን እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ከሻሸመኔ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራም ሊሳካ አልቻለም፡፡ ሙከራችንን እንቀጥላለን።

XS
SM
MD
LG