የሮማ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ፣ አቅመ-ደካማ ፣ በዓለም የተዘነጉ ፣በግዛታቸው ባለው መቋጫ ያላገኘ ጦርነት ምክንያት ፣ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና የተፈናቀሉ ሰዎች በረሃብ እንዲቆራመዱ የሆነባቸው ሁለት የአፍሪካ ሀገራትን ከማክሰኞ ጀምረው እንደሚጎበኙ ታውቋል።
ከአውሮጳዊያኑ ጥር 31-እስከ የካቲት 5 ባለው ጊዜ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎን እንዲሁም ደቡብ ሱዳንን ይጎበኛሉ። የአሁኑ ጉብኝት የ86 ዓመቱ ሊቀ-ጳጳስን ከህዝባቸው መካከል ግማሹ ካቶሊክ በሆነባቸው፣ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን በጤና ፣ በትምህርት ስርዓት እና በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድ ቁልፍ ሚና በምትጫወትባቸው በእኒህ ሀገራት እንደሚያቆያቸው ተነግሯል ።
የአሁኑ ጉብኝት ባለፈው ሀምሌ እንዲከናወን የተቃደ ቢሆንም ፣ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ ስር የሰደደ የጉልበት ህመም ስለገጠማቸው ተራዝሟል። አሁንም ድረስ ተሽከርካሪ ወንበር እና ምርኩዝ የሚጠቀሙት ፍራንሲስ የጉልበታቸው ላይ ህመም በእጅጉ እየተሻሻለ መሆኑ ተሰምቷል ።
ሁለቱ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብቶች የታደሉ ናቸው ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ(ዲ አር ሲ) በማዕድናት -ደቡብ ሱዳን ደግሞ በነዳጅ ዘይት ። ይሁንና ሁለቱም ሀገራት በደህነት እና ግጭቶች ተጎሳቁለዋል ።
ከአፍሪካ ሀገራት በስፋት ሁለተኛ የሆነችው እና 90 ሚሊየን የሚሆን የህዝብ ቁጥር ያላት ዲ አር ሲ ፣ የቀድሞው የሮማ ሊቀ-ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ በአውሮፓዊያኑ 1985 ዓመተ-ምህረት ፣ሀገሪቱ ዛዬር ተብሎ በምትጠራበት ዘመን ፣ ካደረጉት ጉብኝት ወዲህ በሊቀ-ጳጳስ ስትጎበኝ የመጀመሪያው ይሆናል።
ፍራንሲስ ምስራቃዊቷን ከተማ ጎማን የመጎብኘት ዕቅዳቸው ፣ በ ኤም 23 አማጽያን እና በመንግስቱ መካከል ግጭት በማንሰራራቱ ተሰርዟል። በዚህ ስፍራ የጣሊያኑ አምባሳደር እና ጠባቂያቸው በአውሮፓዊያኑ 2021 በተከፈተባቸው ጥቃት ተገድለዋል። ፍራንሲስ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ቆይታ በማድረግ የምስራቁ ግጭት ሰለባዎችን ያነጋገራሉ ።
በተመሳሳይ ሊቀ-ጳጳስ ፍራንሲስ የከፍተኛ የኃይማኖት አባቶች ስብስብ አስከትለው ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚያቀኑ ሮይተርስ ዘግቧል ።
በደቡብ ሱዳን 2.2 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲኖሩ፣ 2.3 ሚሊየኑ ደግሞ ሀገር ለቀው ተሰደዋል ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን " ግጭት በአየለባቸው ቀጠናዎች ሰላም ሰላም እና እርቅ በማምጣት ረገድ ኃያል እና ፈጣን ኃይል " እንዳላት በመጥቀስ አሞግሷል ።