በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባልደረቦቻቸው በመገደላቸው የተቆጡ የሄይቲ ፖሊሶች የጠቅላይ ሚንስትሩን መኖሪያ ቤት ወረሩ


ዋና ከተማ ፖርት ኦ ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ
ዋና ከተማ ፖርት ኦ ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ

ባልደረቦቻቸው በታጠቀ ወንጀለኛ ቡድን በመገደላቸው የተቆጡ ብዛት ያላቸው የሄይቲ ፖሊሶች ትናንት ሐሙስ ዋና ከተማዋ ፖርት ኦ ፕሪንስ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ ግድያውን እና የፖሊሶቹን ተቃውሞ ተከትሎ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ፍርሃት መንገሡ ተዘግቧል፡፡

“ፖሊስ” የሚል የተጻፈበት ጥቁር ቲ ሸርት የለበሱት ተቃዋሚ ሰልፈኞች የጠቅላይ ሚንስትር አሪየል ሄንሪን መኖሪያ ቤት ወርረው ያጠቁ ሲሆን ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሱ አልታወቀም፡፡ ፖሊሶቹ በመቀጠል ጠቅላይ ሚንስትሩ በአርጀንቲና በተካሄደ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተካፍለው እየተመለሱ ወደነበረበት ወደ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያው አምርተዋል፡፡

የቪኦኤ የክሪዮል ቋንቋ ዘጋቢ ከጠቅላይ ሚንስትሩ መኖሪያ ቤት ባስተላለፈው ዘገባ ብዙ የተኩስ ድምጾች ይሰሙ እንደነበር ገልጾ የተገደለ ወይም የቆሰለ ሰው ይኖር እንደሆን ለማወቅ እንዳልቻለ ጠቅሷል፡፡፡

ወደአውሮፕላን ጣቢያው መግቢያ መንገድ በሚነዱ ጎማዎች ተዘግቶ የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአውሮፕላን ወርደው በዲፕሎማሲያዊ ማረፊያው ንግግር ሊያሰሙ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ ፖሊሶቹ ክፍሉን ወርረውታል፡፡ የጥበቃ አካላት ጠቅላይ ሚንስትሩን ለደህንነታቸው ወደሌላ ስፍራ እንደወሰዷቸው እና ምሽት ላይ መኖሪያ ቤታቸው እንዳስገቧቸው ታውቋል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ፖሊሶች በብሄራዊ የፖሊስ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ጽህፈት ቤት ፊት ለፊትም ጎማ ያቃጠሉ ሲሆን ለባልደረቦቻቸው ክብር የሄይቲን ባንዲራ ዝቅ አድርገው ሰቅለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት “ቪቴል ኦም” የተባለው የወንጀል ቡድን አባላት አራት ፖሊሶችን ሲገድሉ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ደግሞ ሊያንኩርት በተባለች ከተማ ሌሎች ሰባት ፖሊሶች ሳቪየን በተባለው የወንጀል ቡድን ተገድለዋል፡፡ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ፖልሲ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “በፖሊስ ሰራዊቱ የአመራር ለውጥ መደረግ ነበረበት” ብለዋል፡፡

“ተቃዋሚዎቹን እና የተገደሉትን ፖሊሶች ቤተሰቦች እንደግፋለን፡፡ ተናደናል ምክንያቱም ከወንጀለኛ ቡድን አባላት ጋር የተሳሰሩ ፖሊሶች አሉ፡፡ ጥቃት ሲደርስ ዝም ብለው ዳር ቆመው ይመለከታሉ፡፡ የፖሊስ ባለስልጣናቱም ብዙውን ጊዜ ኃላፊነት አይወስዱም፡፡ ይሄ መቀየር አለበት” ብለዋል፡፡

የቀድሞ የሄይቲ ሴኔተር ሟዚ ዣን ቻርልስ ከሄይቲ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ትናንት በዋና ከተማዋ ስለተከሰተው ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

“ጠቅላይ ሚንስትር አሪየል ሄንሪ በእሳት እየተጫወቱ ነው፡፡ ዛሬ የተከሰተው ነገር አስተዳደሩ ችሎታ እንደሌለው የሚያሳይ ነው” ብለዋል፡፡

የተመድ ዋና ጸኃፊ የሄይቲ ልዩ ተወካይ አምባሳደር ሄለን ሚገር ለጸጥታ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር የሄይቲ ፖሊስ ሠራዊት በወንጀል ቡድኖች የሚፈጸመውን ሁከት ለመታገል የሚረዳቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መመደብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG