በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋንግ ጉብኝት፤ ቻይና፣ ምዕራብ፣ አፍሪካ


የጋንግ ጉብኝት፤ ቻይና፣ ምዕራብ፣ አፍሪካ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:54 0:00

የቻይና አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በመጀመሪያው የውጭ ጉዟቸው በዚህ ሣምንት አፍሪካን ጎብኝተው አምስት ሃገሮችን አይተዋል።

ሃገራቸው አፍሪካን በምዕራብና በቤጂንግ መካከል ያለ አዲስ ትንቅንቅ መድረክ የማድረግ ሃሳብ እንደሌላትም በአፅንዖት ተናግረዋል።

ቻይና አዲስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሾመች ቁጥር ይህ የሃገሪቱ ቁንጮ ዲፕሎማት የመጀመሪያ የውጭ እግሩ የሚያርፈው አፍሪካ ላይ ነው። ይኸው ከሰላሣ ዓመት በላይ ተቆጠረ ይህንን አያያዝ ቻይና ወግና ልማድ ካደረገች። ቺን ጋንግም ባለፈው ሰሞን አዲሱን ሥራቸውን ሲጀምሩ ያንኑ ልማድ ነው የተከተሉትና ያስቀጠሉት።

ቤጂንግ ባለፉ ቅርብ ዓመታት ውስጥ በዘረጋችው የመቀነትና መንገድ መርኃግብሯ አማካይነት አፍሪካ ላይ እጀግ የበዛ ወረት አፍስሳለች።

አሁን ታዲያ አሜሪካ ለአፍሪካ በያዘቻቸው ትልሞች ቻይና ላይ ለመድረስ ብርቱ ሩጫ ውስጥ መግባቷን አንዳንድ ተንታኞች ይጠቁማሉ። ባለፈው ወር፣ ታኅሣስ ውስጥ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካን መሪዎች ዋሺንግተን ላይ ጠርተው ሰብስበው ነበር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን በዚህ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያ የነበሩ ጊዜ ‘ቻይና አፍሪካ ውስጥ ከአሜሪካ ጋር ግብግብ አልገጠመችም’ ሲሉ የሃገራቸው ቴሌቪዥን አሳይቷል።

“አፍሪካ የምትፈልገው የጎራዎችን ግብግብ ሳይሆን አጋርነትና ትብብር ነው። የአፍሪካ ሃገሮች ከዚህ ወይም ከዚያ ጎራ ጋር እንዲወግኑ ሊያስገድዳቸው የሚችል መብት ያለው አንድም ሰው ወይም ሃገር የለም” ብለዋል።

ቺን በዚሁ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ውስጥ ሰማንያ ሚሊየን ዶላር የወጣበትን የአርሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል መርቀዋል። ‘የቻይና ገፀ-በረከት ወይም ችሮታ ነው’ ተብሏል።

የማዕከሉ መመረቅ ለቻይና ‘የዲፕሎማሲ ድል ነው’ ይላሉ የአፍሪካ ሥልታዊ ጥናቶች ማዕከል ባልደረባው ፖል ናንቱይላ ጆበርግ፤ ደቡብ አፍሪካ ካለችው የዚህ ዘገባ አጠናቃሪ ኬት ባርትሌት ጋር በስካይፕ ሲነጋገሩ። “በቺን ጋንግ ጉብኝት አንዳንድ መልክዕክቶችን ለማስተላለፍ ተፈልጓል - አሉ ናንቱይላ - አንዱም በቻይናና በአፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት የተረጋጋ፣ ገፀ-ብዙና ሥር የያዘ እንደሆነ ማሳየት ነው።”

ቺን ለጊዜው ምን ያህል እንደሆነ ያልተገለፀ ዕዳ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ ማንሳታቸውን አስታውቀዋል። የሁለቱ ዓመታት ጦርነት ያጎሳቆላትን ትግራይን መልሶ ለመገንባት ጉዳይ የሚውል ገንዘብ ሃገራቸው እንደምሰጥም ቃል ገብተዋል።

አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫና የመሻር አቅም ያለው ድምፅ እንዲኖራት የያዘችውን ዘመቻ ቻይና እንድትደግፍ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ቺን ጋንግን ጠይቀዋል።

“አፍሪካ አህጉር አንድ ቢሊየን ሦስት መቶ ሚሊየን ህዝብና ሃምሣ አራት ሃገሮችን ይዞ የዚህ ዓለምአቀፍ አስተዳደር አካልና የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ቋሚ አባል የመሆን መብት አለው” ብለዋል ሊቀመንበሩ።

ቺን የኢትዮጵያ ጉዳያቸውን ሲጨርሱ ተነስተው ወደ ቤኒንና ወደ ጋቦን ሄዱ። ይሄ ደግሞ ቻይና በፈረንሣይ አፍ የሚናገሩ አፍሪካዊያን ዘንድ ለመዝለቅ የሚያስችላትን የመቀነትና መንገድ መርኃግብሯን የማስፋፊያ ግብ መንደርደሪያ እንደሆነ ተሰምቷል።

ከዚያም ቁልፍ የደኅንነትና የፀጥታ አጋሯ ወደሆነችው አንጎላ ጎራ ብለዋል። ከዚያም እጅግ በበዛ የንግድና የመዋዕለ-ነዋይ ትሥሥራቸው ምክንያት ወዳጅነታቸው ጠበቅ ወዳለውም ግብፅ በርረዋል። ግብፅ ውስጥ ከካይሮ ወጣ ብሎ በሚገኘው አዲስ የአስተዳደር ዋና ከተማ ግንባታ ውስጥ ቤጂንግ አለች፤ በስዊዝ መተላለፊያ የባህር ወሽመጥ ሥራ ውስጥም ቤጂንግ አለች። ግብፅ ለቤጂንግ ስትራተጂያዊ ማማተሪያ ነች።

ቺን እዚያው ካይሮ ሳሉ ያገኙት የግብፅን ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆን የአረብ ሊግንም አነጋግረዋል። የእሥራኤልና የፍልስጥዔም መቆራቆስና ደም መፋሰስ እንዲያበቃ ሃገራቸው ‘አላት’ ያሉትን ‘ብርቱ ፍላጎት’ ነግረዋቸዋል።

‘ምናልባት ምናልባት ቺን ለየት ያሉ ዓይነት ዲፕሎማት ሳይሆኑ አይቀሩም’ ከሚሉ ተንታኞች ሠፈር የደቡብ አፍሪካው የዓለምአቀፍ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ባልደረባዋ ሎረን ጆንስተን በስካይፕ እንዲህ ብለዋል... ‘በዩናይትድ ስቴትስ የሃገራቸው አምባሳደር በነበሩ ጊዜ የሚሰጧቸው መግለጫዎች ኃይል የመቀላቀል ነገር ይስተዋልባቸው ነበር። ምናልባት ከዩናይትድ ስቴትስ ሲወጡ ከእነዚያ የፖሊሲ ክበቦች ጋር ሊሠሩ የሚችሉባቸውን የራሳቸውን መንገዶች ተልመው ሊሆን ይችላል። ከዚያ በመነሳት በዓለምአቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ የተለዩ የአመለካከት አቅጣጫዎችና ሃሳቦች ይኖሯቸውም ይሆናል።

ቺን ጉዳያቸውን ፈጣጥመው ሲወጡ ከዋሺንግተን የገንዘብ ሚኒስትሯ ጃኔት የለን ሦስት ሃገሮችን ለመጎብኘት አፍሪካ ገብተዋል።

ይኸን ጊዜ አንዳንድ ዘጋቢዎች እንዲህ አሉ ‘አሃ! የአፍሪካ ጂዖፖለቲካዊ ትርጉምና ፋይዳ እያንፀባረቀ ይሆን እንዴ?!’

XS
SM
MD
LG