በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ራስን ማጥፋት የአይምሮ ጤና ቀውስ ውጤት ነው


ራስን ማጥፋት የአይምሮ ጤና ቀውስ ውጤት ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:14:58 0:00

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተደጋጋሚ ይሰማል። ማህበራዊ ሚዲያው ከቀደመው ጊዜ የበለጠ መረጃዎችን እንድንሰማ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ፣ ራስን ማጥፋትን በተመለከተ ጥናት ያጠናው የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በየእለቱ 30 ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያጠፉና በዚህም ምክንያት ቢያንስ 150 ሰዎች ቀሪ ህይወታቸውን የሚወዱት ሰው ራሱን በማጥፋቱ በሚያስከትለው መዘዝ ጥላ ስር እንደሚያሳልፉ አመልክቷል።

ሄኖክ አምዴ አካለወርቅ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ድረጃ ትምህርቱንም ሊሴ ገብረማሪያም እና ግሪክ የተሰኙ የግል ትምህርት ቤቶች ተምሯል። ወላጆቹ እሱን እና ወንድሙን ያሳደጓቸው በፍቅር እና በእንክብካቤ ነው። ሆኖም ሄኖክ ከልጅነቱ ጀምሮ ሌሊት እንቅልፍ በሚነሱ፣ በሚያስጨንቁ እና በሚረብሹ ስሜቶች አይምሮው እረፍት ያጣ ነበር። ሄኖክ እንደሚለው ወላጆቹ ይህን ችግሩን ቢያስተውሉትም፣ ትኩረት ሰጥተው ግን ወደ እርዳታ አልወሰዱትም።

ሄኖክን በልጅነት እድሜው ሰላም ያሳጣው አስፈሪ እና አስጨናቂ ስሜት፣ እንዲሁም በዚህ ምክንያት የደረሰበት እንቅልፍ የማጣት ችግር እያደገ ሲመጣ በሌሎች ሱሶች ተተካ። ለዚህ ደግሞ ሄኖክ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቅሰው የሚወዳቸው እናት አና አባቱ ትዳር መፍረስ ነው።

በቤተሰባችን ውስጥ ይፈጠራል ብሎ ያልጠረጠረው ፍቺ ያስደነገጠው ሄኖክ መደበቂያውን በተለያዩ እንደ አልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ እፆች የመሳሰሉ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገር ውስጥ አደረገ። ሆኖም ከሚያስጨንቁት ሀሳቦች እና የሚረብሹት ስሜቶች ለመላቀቅ የመረጠው ሱስ ግን በጊዜ ሂደት ወደ ሥነ-ልቦና ስብራት እና ተስፋ መቁረጥ አምርቶ በመጨረሻ ራሱን የማጥፋት ሙከራ አደረገ።

ሄኖክ "እግዚአብሄር ቀንህ አይደለም ስላለኝ ከሞት አተረፈኝ" ይላል ራስን የማጥፋት ሙከራው ከሽፎ በህክምና ድጋፍ ስለመትረፉ ሲያወራ። ነገር ግን ልክ እንደሄኖክ ሁለተኛ እድል ያላገኙ፣ በተለያዩ ምክንያቶች የአይምሮ ጤና መቃወስ አጋጥሟቸው እርዳታ ባለማግኘታቸው ራሳቸውን ያጠፉ እና እስከወዲያኛው ያሸለቡ በርካቶች ናቸው።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተለያዩ ሰዎች ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ተደጋግሞ ይሰማል። የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ከአመት በፊት ባጠናው ጥናት መሰረትም ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ 30 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ። ለመሆኑ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉት ለምንድን ነው? ዶክተር ኤልያስ ገብሩ የአይምሮ ጤና ሀኪም እና አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ አርምሞ የተሰኘ የማሰልጠኛ ማዕከል ባለቤት ሲሆኑ በአይምሮ ጤና ዙሪያ አምስት መፅሃፎችን አሳትመዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ጥናት ራስን ማጥፋት በተለያዩ ምክንያቶች ሊደርስ እንደሚችል ይዘረዝራል። በግል ህይወት ውስጥ የሚደርሱ ሁነቶች፣ ከማህበረሰብ መነጠል የመሳሰሉ ማህበራዊ ክስተቶች፣ ወይም በአካባቢ የሚከሰቱ እንደ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ራስን ለማጥፋት የሚያደርስ የአይምሮ ህመም መከሰት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ዶክተር ኤርሚያስ ራስን ማጥፋት በማንኛውም የኑሮ ድረጃ ያለ ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ያሰምሩበታል።

ሄኖክ ከራሱ ልምድ በመነሳት፣ አንድ ሰው የራስ ማጥፋት ውሳኔ ላይ የሚደርሰው የደረሰበት የአይምሮ መቃወስ እርዳታ ሳያገኝ ከቁጥጥር ውጪ ሲሆን መሆኑን ያስረዳል። ዶክተር ኤርሚያስም የሚያስረዱት ራስ ማጥፋት በአንድ ግዜ የሚደረስ ውሳኔ አለመሆኑን ነው።

ዶክተር ኤርሚያስ በጊዜ ህክምና ባለማግኘት ምክንያት ራስን ወደ ማጥፋት ሊከቱ የሚችሉ የአይምሮ ህመሞች መረበሽ፣ ድብርት፣ ሱስ የሚያሲዙ ነገሮችን አላግባብ መጠቀም እና የመሳሰሉት መሆናቸውን ይገልፃሉ።

አገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ችግሮች በተበራከቱበት ዓለም የሚኖሩ ወጣቶች ከችግሮቻቸው ለመሸሽ የመጀመሪያ መደበቂያ አድርገው የሚመርጡት ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮችን ነው። ሄኖክ ይህ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ አስፈሪ ሁኔታ ላይ ደርሷል ሲል ስጋቱን ያጋራል።

ይህ ብቻ አይደለም፣ ዶክተር ኤሊያስ በስፋት በሀገር ደረጃ የሚከሰቱ እንደ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ጦርነት የመሳሰሉ ችግሮችም ለግለሰቦች አይምሮ ጤና መቃወስ ምክንያት እንደሚሆኑ ያሰምሩበታል።

ሄኖክ አሁን ከደረሰበት የአይምሮ ጤና መታወክ አገግሞ ያለፈበትን ፈተና የሚያሳይ፣ እንዲሁም ስለአይምሮ ጤና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እና መንገዶችን የሚያመላክት "ወደ ራስ መመለስ" የተሰኘ መፅሃፍ ፅፎ አሳትሟል። የዩቲዩብ ገፅ በመክፈትም ተሞክሮዎቹን ያጋራል፣ ባለሙያዎችን እና ሌሎች የህይወት ልምዳቸውን የሚያካፍሉ ግለሰቦችን ያነጋግራል።

ከቤተሰብ ድጋፍ ጎን ለጎን ሌሎችም ሰዎች ራስን ወደማጥፋት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ምን አይነት እርዳታ ማግኘት አለባቸው ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ኤልያስም መልስ አላቸው።

የኢትዮጵያ ህክምናት ማህበርም ሆነ ሌሎች በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአእምሮ ጤንነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ተገቢውን እርዳታ በጊዜ ካገኙ ሊሻላቸው እና ሙሉ ለሙሉ ሊያገግሙ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ሄኖክ ምስክር ነው።

XS
SM
MD
LG