አሊ ሬዛ አክባሪ የቀድሞ የኢራን ምክትል መከላከያ ሚኒስቴር የነበሩ ሲሆን ለእንግሊዝ ስለላ ያካሂዳሉ በሚል ተከሰው ነበር። አክባሪ በስቅላት መሞታቸውን ሚዛን የተሰኘው የኢራን ዜና ወኪል ዛሬ ያስታወቀ ሲሆን ቅጣቱ መቼ እንደተፈፀመ ግን አልተገለፀም።
አክባሪ እ.አ.አ ከ2019 አንስቶ እስር ላይ የነበሩ ሲሆን እንግሊዝ እና አሜሪካ ኢራን የሞት ቅጣቱን ተፈፃሚ እንዳታደርግ ሲወተውቱ ቆይተዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ የሆነው አምረንስቲ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት የአክባሪ በሞት መቀጣት የኢራን ባለስልጣንት በህይወት የመኖር መብት ላይ የሚያደርሱትን አስከፊ ቅጣት ያሳይል ብሏል።
በተመሳሳይ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በትዊተር ገፃቸው ላይ "ይህ ለራሱ ህዝብ ሰብዓዊ መብት ክብር በሌለው መንግስት የተፈፀመ ርህራሄ የሌለው የፈሪዎች ድርጊት ነው" ሲሉ አስፍረው በሁኔታው መደንገጣቸውን ገልፀዋል።
የሞት ቅጣቱ ከመፈፀሙ በፊት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ቃል አቀባይ ቬዳንት ፓቴል በሰጡት መግለጫ "በአሊ ሬዛ አክባሪ ላይ የቀረበው ክስ እና የሞት ቅጣት ፍርድ ፖለቲካዊ ነው፣ የሱ መገደል የማይታሰብ ነው" ብለው ነበር።
አንዲት ወጣት ሴት የራስ መሸፈኛዋን ያለአግባብ በመልበሷ ከታሰረች በኃላ ህይወቷ ማለፉን ተከትሎ መላውን ኢራን ወጥሮ የያዘ ተቃውሞ በመነሳቱ ኢራን የሞት ቅጣቶች እየፈፀመች ሲሆን ተቃውሞው ከተነሳ ወዲህ ቢያንስ አራት ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል።