በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የከባድ መሳሪያዎች ርክክብ መደረጉን የህወሓት ቃል አቀባይ ገለፁ


ፎቶ ፋይል የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ኅዳር 3/2015 ዓ.ም /ኤፒ
ፎቶ ፋይል የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ ኅዳር 3/2015 ዓ.ም /ኤፒ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሃት ከሁለት ወራት በፊት ያደረጉትን ስምምነትን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዳስረከቡ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገፃቸው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ወክለው በርክክቡ ላይ የተገኙት ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በበኩላቸው፤ "በውሉ መሰረት ከትግራይ ኃይሎች በአጉላ የተሰበሰቡ የጦር መሳሪያዎችን ቆጥረን ተረክበናል" ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን የሚከታተልና የሚቆጣጠረው የአፍሪካ ኅብረት ቡድን የከባድ የጦር መሳሪያዎች ርክክብ መጀመሩን መታዘቡን ገልጿል።

አቶ ጌታቸው ዛሬ ማለዳ በለቀቁት የትዊተር መልዕክት የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪ ቡድን ከባድ መሣሪያዎቹን ማስረከባቸውን አረጋግጠዋል። “የሠላም ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ሲሉም ተስፋቸውን አስፍረዋል።

ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጎን ሲዋጉ የነበሩትና በሰላም ስምምነቱ ያልተሳተፉት የጐረቤት ኤርትራ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ የትግራይ ኃይሎች ሲወተውቱ መቆየታቸውን ያስታወሰው የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ የኤርትራ ኃይሎች ግን አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች እንዳሉ የዐይን እማኞች እንደነገሩት ገልጿል።

በዩናይትድ ስቴትስና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተመራማሪዎችን ጥናት መሰረት በግጭቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ይገመታል።

አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ወደ ሚኖሩበት የትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ በረራ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደገና ቀጥለዋል።

/ዘገባው ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል/

XS
SM
MD
LG