በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ መንግስት እና አልሸባብ "ንግግር ጀምረዋል" መባሉን አስተባበሉ


 ምስሉ በጥቅምት 29/2022 ሞቃዲሹ ውስጥ በደረሰ የአልሸባብ ጥቃት የተጎዳ ሰላማዊ ሰው በእርዳታ ሰራተኞች ከአካባቢው እንዲርቅ ሲደረግ ያሳያል።
ምስሉ በጥቅምት 29/2022 ሞቃዲሹ ውስጥ በደረሰ የአልሸባብ ጥቃት የተጎዳ ሰላማዊ ሰው በእርዳታ ሰራተኞች ከአካባቢው እንዲርቅ ሲደረግ ያሳያል።

የሶማሊያ መንግስት እና የአልሸባብ ታጣቂዎች ቡድን የሰላም ንግግር እያደረጉ ነው መባሉን አስተባበሉ። ማስተባበያው የተሰማው አብዱልፋታህ ካሲም ሞሃመድ የተባሉ የሀገሪቱ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር እና የህዝብ እንደራሴ ቅዳሜ ዕለት የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ጥያቄ ማቅረቡን መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

አንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ቆየት ብለው መንግስት ከታጣቂው ቡድን "ጥያቄ ቀርቦለታል" መባሉን አስተባብለዋል። " ከቡድኑ ምንም አይነት ጥያቄ አልቀረበልንም "፣ ያሉት የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሼክ አሊ ሚኒስትሩ በተሳሳተ መንገድ ንግግራቸው እንደተወሰደ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

በአልሸባብ ላይ የሶማሊያ መንግስት ያለው አቋም እንዳልተለወጠም አክለዋል።
“እንደ ቡድን ከእነርሱ ጋር እየተደራደርን አይደለም ። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ከቡድኑ መለየት የሚሹ ፣ በሂደት ውስጥ አልፈው የመንግስትን ምህረት ማግኘት ይችላሉ" ፣ ሲሉ አክለዋል- በዋትሳፕ አውታር በኩል በላኩት መልዕክት ።
አልሸባብ በበኩሉ ከመንግስት ጋር ንግግር ተደርጓል መባሉን አስተባብሏል።ከቡድኑ ጋር ትስስር ያለው ድረ-ገጽ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ የተናገሩለት የሰላም ንግግር መሰረተ ቢስ ነው ብሏል።

"በመካከላችን ንግግር እንደሌለ ፣ንግግርም እንደማይኖር አረጋግጣለሁ" ሲሉ ማንነታቸው ያልተገለጸ የቡድኑ አመራር ለድረ-ገጹ መናገራቸው ተዘግቧል።


በጥር 2018 የአውሮፓዊያኑ ዘመን ፣ አሊ ድሬ በመባል የሚጠሩት የቡድኑ ቃል አቀባይ ፣"የሰላም ንግግር ከጅምላ ጨራሽ መሳሪያ በላይ የበለጠ አደገኛ ነው " ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል ።

XS
SM
MD
LG