በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ


የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:24 0:00

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት፣ ልደታ ምድብ ችሎት በአቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ ስር ጉዳያቸው ሲታይ በነበሩ ዘጠኝ ተከሳሾች ላይ ዛሬ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀድሞ የብሔራዊ የመረጃ ደህንነት አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን እና በደህንነት ተቋሙ ውስጥ የሥራ ኃላፊ የነበሩት አቶ አማኑኤል ኪሮስ እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት ከአራት ወር የእስር ቅጣት ወስኖባቸዋል፡፡

በዚህ የክስ መዝገብ ስር ሲከራከሩ በቆዩ ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ላይም ከሦስት እስከ አራት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት የወሰነባቸው ሲሆን፣ ከነሱ መሃከል ሦስቱ የእስር

ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው ዛሬ እንዲፈቱ ወስኗል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታኅሣስ 7/2015 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በሰጠበት ጊዜ አቶ መዓሾ ኪዳነ እና አቶ ተሾመ ኃይሌ የተባሉ ሁለት ተከሳሾች ከአራት ዓመት ክርክር በኋላ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች ከተያዙበት ከጥቅምት 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ ከአራት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ታስረው በመቆየታቸው፣ አቶ ያሬድ ዘሪሁንን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች በሁለት ቀናት ውስጥ በአመክሮ ከእስር እንደሚለቀቁ ከጠበቆቻቸው አንዱ አቶ ክፍላይ መሓሪ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ጉዳያቸው ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር እንደሚያያዝ በመገለፁ፤ የመነሻ ክሳቸው ተቀይሮ በወንጀል ሕግ እንዲከላከሉና እንዲዳኙ መደረጉን የሕግ አማካሪው አቶ ክፍላይ ጠቅሰዋል፡፡

XS
SM
MD
LG