በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪ ቡድን አባላት መቀሌ ናቸው


የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ የቡድኑ አባል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታና የሰላሳ ሁለት ሀገሮች አምበሳደሮችና ተወካዮችም መቀሌ ናቸው።
የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ የቡድኑ አባል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታና የሰላሳ ሁለት ሀገሮች አምበሳደሮችና ተወካዮችም መቀሌ ናቸው።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሃት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የሚገመግመውና የሚከታተለው የአፍሪካ ኅብረት ቡድን በመቀሌ ከተማ ተገኝቶ በዛሬው ዕለት ብይፋ ሥራውን ጀምሯል።

የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፣ የቡድኑ አባል የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታና የሰላሳ ሁለት ሀገሮች አምባሳደሮችና ተወካዮች በተገኙበት በዚሁ የምሥረታ መድረክ ላይ የዩናይትስ ስቴትስና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮችም ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች፣ የትግራይ ክልል አመራሮችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮችም ተገኝተዋል።

ዋና አደራዳሪው ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ መቀሌ ሲገኙ ለ10ኛ ጊዜ መሆኑን ገልፀው፤ የሰላም ስምምነቱን የሚገመግምና የሚከታተል ቡድን ሥራ መጀመሩ ስምምነቱ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው፤ በሁለቱም በኩል መተማመን እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካንን ወክለው የተናገሩት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ "ለሀገሬ ሰዎች ሁሉ የሰላም አየር ይሁንልን" በማለት ምኞታቸውን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዛሬ መቀሌ መግባቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።ተልዕኮውም በትግራይ ክልል የሚገኙና በፌደራል መንግሥት ስር የሚተዳደሩ አየር ማረፊያዎችን እንደዚሁም የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮም ፣ የባንክና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማትን መጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመልክቷል።

ከዚህ ቀደም ብሎም ወደተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመግባት ኅብረተሰቡን ለማረጋጋትና ወደ ቀየው ለመመለስ የሚያስችሉ የፀጥታና ደህንነት የማስከበር ስራዎችን እየሠራ መቆየቱም ጠቁሟል።

በተጨማሪም አንድ የትግራይ ክልል ባለስልጣን አጉላዕ በተባለችና ከመቀሌ በሰሜን አቅጣጫ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ቦታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መግባቱን ለቪኦኤ ገልፀዋል።

በዚህ ቦታ የትግራይ ኃይሎች የፈቱትን ከባድ የጦር መሳርያ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ቆጠራ ያካሂዳሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ታኅሣስ 13 እና 14 /2015 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በናይሮቢ ያደረጉትን ውይይት ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ አደራዳሪ ቡድኑ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከመቀሌ መግለጫ እንደሚሰጡ መግለፃቸውን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።

ቡድኑ በዛሬው ዕለት መቀሌ ከተማ የተገኘው በእቅዱ መሰረት የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ለመገምገም መሆኑ ታውቋል።

/ዘገባው የሙሉጌታ አፅብሃ ነው/

ዘገባው ተጨማሪ መረጃዎች ተካተውበታል

XS
SM
MD
LG