በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ልብ አንጠልጣዩን ጨዋታ በማሸነፍ አርጄንቲና የዓለም ዋንጫን አነሳች


SOCCER-WORLDCUP-ARG-FRA/REPORT
SOCCER-WORLDCUP-ARG-FRA/REPORT

ምትሀተኛው ሜሲ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሲሆን ምባፔ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቀዋል

እጅግ ድራማዊ በሆኑ ክስተቶች የታጀበው 22ኛው የካታሩ የፊፋ የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በአርጄንቲና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ሊዮኔል ሜሲ በነገሰበት፣ ተቀይሮ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ አንጌል ዲማሪያም ድንቅ ብቃቱን ባሳየበት፣ አርጄንቲና በፈረንሳይ ላይ የበላይነቷን ባሳየችበት 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ፣ ዋንጫውን የግሏ አድርጋለች፡፡

አርጄንቲና በምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋ፣ በሳዑዲ አረቢያ ያስተናገደችው ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት የሀፍረት ሳይሆን የብርታት ምንጭ እንደሆናቸው፣ ለፍጻሜ ከደረሱ በኋላ በሰጠው አስተያየት የተናገረው ሜሲ በርግጥም ሽንፈታቸው የወንሄ ምንጭ እንደሆናቸው እና ለድል እንዳበቃቸው ከቡድኑ አባላት ጋር በመሆን በተግባር አሳይቷል፡፡

የመጀመሪያውን የጨዋታ አጋማሽ በሜሲ የፍጹም ቅጣት ምት እና በዲማሪያ ድንቅ ግብ 2 ለ 0 በመምራት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ያመራችው አርጄንቲና፣ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቷን አስቀጥላ መጨረስ አልቻለችም፡፡ ከዕረፍት በኋላ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ፈረንሳዮች ኮከባቸው ካይሊያን ምባፔ በፍጹም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ግቦች አቻ በመሆን፣ ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት አምርቷል፡፡

በተጨማሪ ሰዓት ተጭነው የተጫወቱት አርጄንቲናዎች በምትሀተኛው ኮከባቸው ሜሲ አማካኝነት በ108ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ቢያስቆጥሩም፣ ፈረንሳይ 118ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ በእጅ መነካቱን ተከትሎ ያገኘችውን ፍጹም ቅጣት ምት ምባፔ አስቆጥሮ ጨዋታው 3 እኩል በመጠናቀቁ በፍጹም ቅጣት ምት ተለያይተዋል፡፡ በዚህም አርጄንቲና 4 ለ 2 በመርታት ከ36 ዓመታት በኋላ ዋንጫውን አንስታለች፡፡

እስካሁን በ5 የዓለም ዋንጫዎች ላይ ተሰልፎ የተጫወተው ሜሲ ከነዚህም በሁለቱ ለፍጻሜ ደርሶ፣ ምናልባትም የመጨረሻው በሆነው የዓለም ዋንጫ ለራሱም ለሀገሩም ትልቁ የሆነውን የእግርኳስ ዓለም ስኬት ተጎናጽፏል፡፡

የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የዘንድሮውን የካታር ዓለም ዋንጫ ወስደዋል
የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን የዘንድሮውን የካታር ዓለም ዋንጫ ወስደዋል

አርጄንቲና ከ36 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫዋን በማሸነፍ፣ አጠቃላይ ያሸነፈቻቸውን የዓለም ዋንጫም 3 አድርሳለች፡፡

የ7 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው ሜሲ፣ የዓለም ዋንጫን በማንሳት፣ በእግርኳስ ህይወቱ ያላሳካውን ብቸኛውን እና ትልቁን ስኬት አስመዝግቧል፡፡

ሜሲ በእግርኳስ ህይወቱ የመጨረሻ ድንቅ ብቃቱ ላይ በነበረበት በ2014ቱ የብራዚል የዓለም ዋንጫ ከሀገሩ ጋር ለፍጻሜ ቢደርስም፣ በጀርመን 1 ለ 0 ተሸንፈው ትልቁን ህልሙን ማሳካት አልቻለም፡፡ በሕይወቴ ያላሳካሁት የሚለውን እና ከጸጸት የሚድንበትን፣ ሀገሩም ለዘላለም የምትኮራበትን እና እንድትዘክረው የሚያደርገውን ይህን ህልሙን ታዲያ በካታር ማሳካት ችሏል፡፡

ሜሲ የአርጄንቲና የምንጊዜም ኮከብ ተጫዋችነትን ክብረርንም የ1986ቱን የዓለም ዋንጫ ለሀገሩ ካሳካው ዲያጎ ማራዶና ጋር ተጋርቷል፡፡ የ35 ዓመቱ ሜሲ፣ አሁን በእግርኳስ ህይወቱ ሳላሳካው ቀረሁ የሚለው ምንም አይነት ስኬት የለም፡፡

ሜሲ አሁን የአርጄንቲና ብቻ ሳይሆን የዓለምም ክስተት ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ከምንጊዜም ተቀናቃኙ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያለውን የበላይነት በጉልህ አሳይቷል፡፡ 5 ጊዜ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል የባላንዶር አሸናፊ የሆነው የ37 ዓመቱ ሮናልዶ የዓለም ዋንጫን አንስቶ አያውቅም፡፡

የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ፣ ለተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የ1962ቱን የብራዚል እና የ1938ቱን የጣሊያን ታሪክ መጋራት የምትችልበትን ድንቅ እድል አምክናለች፡፡

ካይሊያን ምባፔ ዛሬ ያስቆጠራቸውን 4 ግቦች ጨምሮ በ9 ግቦች የዓለም ዋንጫው ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ምባፔ በዓለም ዋንጫ ታሪክ በፍጻሜ ጨዋታ ላይ ሀትሪክ የሰራ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆንም ስሙን በታሪክ መዝገብ አስፍሯል፡፡

ሜሲ የዓለም ዋንጫው ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል፡፡ ግብ ጠባቂያቸው ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ ምርጥ ግብ ጠባቂ፣ 24 ቁጥሩ ኤንዞ ፈርናንዴዝ ደግሞ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብለው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡

የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጄንቲና ከፊፋ 42 ሚሊዮን ዶላር በሽልማት መልክ ታገኛለች፡፡

ሁለተኛ የወጣችው ፈረንሳይ፣ ፊፋ ካዘጋጀው 440 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ የሽልማት ገንዘብ ውስጥ 30 ሚሊዮን ዶላር ታገኛለች፡፡

3ኛ የወጣችው ክሮሺያ 27 ሚሊዮን፣ አራተኛዋ ሞሮኮ ደግሞ 25 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማሉ፡፡ በዓለም ዋንጫው የተሳተፉ እያንዳንዱ ቡድኖች በትንሹ 9 ሚሊዮን ዶላር እና የዝግጅት 1.5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማሉ፡፡

XS
SM
MD
LG