በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ "ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጠንካራ መሰረት አለ" - ብሊንከን


በኢትዮጵያ "ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጠንካራ መሰረት አለ" - ብሊንከን
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:55 0:00

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ግጭት መቆሙን፣ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት መሻሻሉን እና መሰረታዊ አገልግሎቶች በድጋሚ መጀመራቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ተናገሩ። ብሊንከን ይህን ያሉት ለሶስት ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ማጠቃላያ ላይ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።


ዩናይትድ ስቴትስ ለሶስት ቀናት ባስተናገደችው እና ትላንት በተጠናቀቀው የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን እና ሌሎች የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የተናጠል ስብሰባዎችን አካሂደዋል። ከብሊንከን ጋር በነበራቸው ቆይታም በዋናነት በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት አመት ሲካሄድ የቆየውን ግጭት ለማቆም በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ ተነጋግረዋል።

የጉባዔውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ትላንት ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት አንተኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መሻሻሎች ማሳየቱን ተናግረዋል።

"ግጭት የማቆም ስምምነቱ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ሁከት እንዲቀንስ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብዓዊ ርዳታ እንዲገባ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ አድርጓል። እናም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በዓለም አቀፍ አጣሪዎች መጣራት ቢኖርበትም፣ ከዚህ በኃላ እየተፈፀሙ እንዳልሆነ ተስፋ እናደርጋለን።"

የሰላም ስምምነቱ በተግባር ላይ መዋሉ ቁልፍ እና መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን እና ስምምነቱ በፍጥነት እና ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑ መረጋገጥ አለበት ያሉት ብሊንከን ሌላኛው የስምምነቱ ቁልፍ ጉዳይ የኤርትራ ሀይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት መሆኑን፣ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ባደረጉት ስብሰባም በአፈፃፀሙ ዙሪያ መነጋገራቸውን አመልክተዋል።

"አሁን ውጥረቶችን ለመቀነስ እና ግጭቶችን ለመፍታት አውንታዊ መሰረቶች ያሉን ይመስለኛል። ለዘላቂ ሰላም ጠንካራ መሰረት አለን። ነገር ግን እነዚህ በቀላሉ ሊሰበሩ ይችላሉ። ስለዚህ የማያቆርጥ ተሳትፎ እና የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃሉ። እናም በዚህ ሳምንት በዋሽንግተን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያደረግነው አንዱ ነገር ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ነው። ስለዚህ በመጪዎቹ ቀናት ብዙ ክትትሎች ይኖራሉ።"


የሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነትን በተመለከተ ትላንት ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሬክ ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ወደትግራይ ክልል የሚሄደው ሰብዓዊ ርዳታ እየተሻሻለ መምጣቱን እና ምግብና ሌሎች አቅርቦቶች ወደ ትግራይ ክልል በሚያስገቡት አራቱም የአፋርና የአማራ ክልል ኮሪደሮች እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እና አጋር ተቋማት ከ1ሺህ 600 በላይ የጭነት መኪናዎችን በማሰባሰብ ከ63 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ከ4ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የጤና፣ የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የጥበቃ አቅርቦቶች እንዲሁም የውሃ፣ እና የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶች መዳረሳቸውንም ገልፀዋል። ዱጃሪክ አክለው የኤሌክትሪክ እና የስልክ መገናኛ መስመሮች አክሱምና ሽሬን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች እድሳት መደረግ መጀመሩ በሰብዓዊ ተግባራት እና በማህበረሰቡ ላይ አውንታዊ ተፅእኖ አለው ብለዋል።


ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት የሀገር ውስጥ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ገበያ ያለ ታሪፍና ኮታ እንዲያስገቡ ከአሜሪካ መንግስት የተሰጣቸው ተጠቃሚነት (አጎአ) እንደተሰረዘች ናት። ከጉባዔው በኃላ ኢትዮጵያ የቀረጥ ነፃ ስምምነቶች ውስጥ ትካተት እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ብሊንከን ሲመልሱ ሀገራቸው በቅርቡ የመጠቀሚያው ግዜ በሚያበቃው አጎዋ ዙሪያ እየተነጋገረች በሆኑን ገልፀዋል።

"አጎዋ የመጠቀሚያው ግዜ ሲያበቃ እንዴት ወደፊት እንደምንቀጥል እያየን ባለንበት ወቅት፣ እንዴት በተሻለ ሁኔታ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አጋር ሀገራት፣ የግሉ ዘርፈና የአሜሪካ ምክር ቤት ጋር እየተነጋገርን ነው። "

የአሜሪካ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ አሜሪካ ከአዲሱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት ጋር አዲስ ከቀረጥ ነፃ እንድሎችን የሚፈጥር የመግባቢያ ሰነድ ፈርማለች። ኢትዮጵያ የዚህ አዲስ እድል ተጠቃሚ ትሁን አትሁን ግን በግልፅ አልታወቀም።


ብሊንከን ትላንት በዋሽንግተን የስብሰባ ማዕከል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካከል በሚታየው ውጥረት ዙሪያ ከሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጋር በጉባዔው ላይ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።


"አሁን ትልቁ ነገር የM23 ተዋጊዎች ወታደሮቻቸውን ወደኃላ መመለሳቸው ነው። ለዛ ደግሞ ሩዋንዳ ያለውን ተፅእኖ ተጠቅሞ ያ እንዲሆን ያበረታታል ብለን እንጠብቃለን። ጎን ለጎን ደግሞ ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ታጣቂ ቡድን መሳሪያውን ማውረድ አለበት። ያ ደግሞ ሩዋንዳ ነፃ አውጪ ቡድን የሆነውን ኤፍ ዲ ኤል አርንም ይጨምራል። የሩዋንዳም ኃይሎች ወደኃላ መመለስ አለባቸው።"


በሶስቱ ቀን ጉባዔ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በነበሩ ስብሰባዎች ከተነሱ አጀንዳዎች መካከል የሩሲያ ቅጥረና ተዋጊ ቡድን የሆነው ዋግነር በአፍሪካ ውስጥ ያለው ተፅእኖ ሲሆን ብሊንከር እንደዋግነር ያሉ ቡድኖች አለመረጋጋትን በመፍጠር እንደሚበዘብዙ፣ መልካም አስተዳደርን እንደሚያዳክሙ፣ የአገሮችን የማዕድን ሀብት እንደሚዘርፉ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን እንደሚጥሱ ተናግረዋል።

"ዋግነር የተሰማራባቸው ሀገራት በሙሉ ራሳቸውን ይበልጥ ደካማ፣ ድሆች፣ ደህንነት የሌለባቸው እና እራሳቸውን ያልቻሉ ሆነው አግኝተውታል። በሁሉም ጋር የምናየው ተመሳሳይ ሁኔታ እና ተመስሳይ ታሪክ ይሄ ነው። ስለዚህ እንደ ዋግነር ያሉ ቡድኖችን መቋቋም እንዲችሉ በአፍሪካ ካሉ አጋሮቻችን ጋር አብሮ መስራታችን አስፈላጊ ነው።"


የአሜሪካ እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ አሜሪካ ለአፍሪካ ያላትን አጋርነት ይበልጥ አጉልታ ያሳየችበት እና አፍሪካ እንደ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክርቤት እና ቡድን 20 የመሳሳሰሉ ሀያልን ሀገራት የሚገኙበት ስብስብ ውስጥ መቀመጫ እንዲኖራት ድምጿን ያሰማችበት ሆኖ ተጠናቋል። በጉባዔው ላይ ቃል የተገቡ ትብብሮች እና 55 ቢሊየን የገንዘብ ድጋፍ ወደ ተግባር እንዲለወጡም ለረጅም ግዜ በአፍሪካ ዲፕሎማቲክ ሆነው ያገለገርሉትን ጆኒ ካርሰን በኃላፊነት ሾማለች።

XS
SM
MD
LG