በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትዊተር የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞችን አገደ


ትዊተር ኩባኒያ
ትዊተር ኩባኒያ

የመናገር ነጻነትን አከብራለሁ ብለው ቃል ገብተው የነበሩት አዲሱ የትዊተር ባለቤት ኢለን መስክ የበርካታ ጋዜጠኞችን ገጾች አገዱ፡፡ ከታገዱት መካከል አንዱ የአሜሪካ ድምጽ የብሄራዊ ጉዳዮች ዋና ዘጋቢ ስቲቭ ኸርማን ይገኝበታል፡፡ ቀድሞ የቪኦኤ የኋይት ሐውስ ቢሮ ኅላፊ የነበረው የስቲቭ ኸርማን የትዊተር ተከታታዮች የትዊተር ገጹን ሲከፍቱ “ታግዷል” የሚል ማስታወቂያ አግኝተዋል፡፡ የሲ ኤን ኤን፡ የኒው ዮርክ ታይምስ እና የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኞች እና የሌሎችም ነጻ ጋዜጠኞች የትዊተር ገጾች ተዘግተው ተመሳሳይ ማስታወቂያ ተለጥፎባቸው ታይተዋል፡፡

ትዊተር የጋዜጠኞቹን ገጾች በምን ምክንያት እንዳገደ ለጊዜው አልታወቀም፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ከትዊተር ኩባኒያ አስተያየት በመጠየቅ በድረ ገጹ ላይ ላሉ አድራሻዎች የላከው ኢ-ሜይል “ሊደርስ አልቻለም” በሚል ማሳሰቢያ ተመልሷል፡፡

የታገዱት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ኤለን መስክ በትዊተር አሰራር ላይ ያደረጓቸውን ለውጦች የሚመለከቱ ዘገባዎች አውጥተዋል፡፡ መስክ ትናንት ሐሙስ ማታ ላይ በትዊተር ባወጡት መልእክት “ ቀኑን ሙሉ ትችት ቢቀርብብኝ ምንም ችግር የለውም፡፡ የት እንዳለሁ መናገር እና ቤተሰቤን ለአደጋ ማጋለጥ ግን ትክክል አይደለም” ብለዋል፡፡

ትዊተር ይህን በሚመለከት ለሁሉም ተጠቃሚ ያወጣው ደምብ ጋዜጠኞችንም ይመለከታል ሲሉ መስክ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኛው ስቲቭ ኸርማን የትዊተር ገጽ መታገዱን አረጋግጦ አንዲከፈትለት ጠይቋል፡፡

XS
SM
MD
LG