በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በድራማዊ ክስተቶች የተሞላው የካታሩ የዓለም ዋንጫ ወደ ፍጻሜው ተቃርቧል


ካታር 2022
ካታር 2022

የምትሀተኛው ሜሲ አርጄንቲና እና በአስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኘው የምባፔ ፈረንሳይ ለፍጻሜው ደርሰዋል፡፡

የአለም ዋንጫው ክስተት የነበረችው ሞሮኮ፣ በግማሽ ፍጻሜው እጇን ሰጥታለች፡፡

የፊታችን ቅዳሜ ሞሮኮ ከክሮሺያ ለደረጃ ሲጫወቱ፣ ዕሁድ ደግሞ የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ፣ ለተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የ1962ቱን የብራዚል ታሪክ ለመጋራት ስትጫወት፣ አርጄንቲናም ለ3ኛ ዋንጫዋ ትፋለማለች፡፡

ከመጀመሪያው ጀምሮ ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስተናገደ የቀጠለው የካታሩ የ2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ 3 ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡

በምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዋ፣ በሳዑዲ አረቢያ ያልተጠበቀ የ2 ለ 1 ሽንፈት ያስተናገደችው አርጄንቲና፣ በኮከቧ ሊዮኔል ሜሲ ተዓምራዊ ብቃት ለፍጻሜው መድረስ ችላለች፡፡

የሳዑዲው ሽንፈት ታዲያ የሀፍረት ሳይሆን የብርታት ምንጭ እንደሆናቸው ሜሲ ለፍጻሜ ከደረሱ በኋላ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ “ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጨዋታ በሳዑዲ እንሸነፋለን ብለን ፈጽሞ ባንጠብቅም፣ ለፍጻሜው ለመድረሳችን ግን ቁልፍ ሚና ተጫውቷል” ሜሲ ከማክሰኞው ድል በኋላ የተናገረው ነው፡፡

አርጄንቲና የ2018 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችውን ክሮሺያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ነው ለፍጻሜው የደረሰችው፡፡

ባለፉት ሁለት ዙሮች ከመመራት ተነስታ ጃፓንን እና ብራዚልን በፍጹም ቅጣት ምት የረታችው ክሮኤሺያ፣ ከአርጄንቲና ጋር ግን ይህን ድል መድገም አልተቻላትም፡፡ ውጤቱን ለመቀልበስ በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ያደረገችው ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራም ፍሬ ሊያፈራላት አልቻለም፡፡

ውጤቱን ተከትሎ የአርጄንቲና ደጋፊዎች የዋና ከተማዋን ቦነስ አይረስ ጎዳናዎች እና አደባባዮች አጥለቅልቀው ደስታቸውን ሲገልጹ፣ የሜሲን ስም እያነሱ ሲዘምሩ ውለዋል፡፡

ሌላኛውን የፍጻሜ ተፋላሚ ለመለየት ትላንት ረቡዕ የተካሔደው የሞሮኮና ፈረንሳይ ጨዋታ ደግሞ፣ በዓለማችን ታላቁ የእግር ኳስ ውድድር የሞሮኮን ያልተጠበቀ ታሪካዊ ጉዞ የገታ ሆኗል፡፡

ፈረንሣይ የአፍሪካን እና የዓረቡን ዓለም የመጀመሪያዋን የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ 2-0 አሸንፋለች፡፡ ገና በ5ኛው ደቂቃ ቲዎ ሄርናንዴዝ ያስቆጠራት ግብ፣ ሞሮኮዎች ጠንካራውን የተከላካይ መስመራቸውን ጭምር ወደ ፊት እያንቀሳቀሱ እንዲጫወቱ ያስገደደች ብትሆንም፣ አስደናቂው የማጥቃት ጥረታቸው ውጤታማ አልሆነም፡፡ ተቀይሮ የገባው ራንዳል ኮሎ ሙአኒ በ79ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ደግሞ የሞሮኮን ተስፋ ያጨለመች ሆናለች፡፡ ሁለቱንም የግብ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው፣ በድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ወጣቱ የፒኤስጂ አጥቂ ካይሊያን ምባፔ ነው፡፡

የመጨረሻው ፊሽካ ሲነፋ፣ በጨዋታ ብልጫ የነበረው ቡድናቸው ተሸንፏልና፣ በሺዎች የሚቆጠሩ፣ የአል ባይት ስታዲየምን በቀይ ቀለም ያጥለቀለቁ የሞሮኮ ደጋፊዎች ሲያነቡ ታይተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በቡድናቸው እዚህ ድረስ መጓዝ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን “ሻምፒዮኖች እንደሆንን እንቆጥራለን ሲሉ የአትላስ አምበሶቹ ደጋፊዎች ተናግረዋል፡፡

የሞሮኮ ተጫዋቾች፣ የቡድኑ አባላት እና ደጋፊዎች፣ ለአሰልጣኛቸው ዋሊድ ሬግራጉይ ከጨዋታው በኋላ ረዘም ያለ እና በአድናቆት የተሞላ ጭብጨባ ቸረውታል፡፡

የሞሮኮ ጉዞ መላውን ዓለም ያስደነቀ በተለይም የአፍሪካንእና የዓረቡ ዓለም ድጋፍ የተቸረው ነው፡፡ ከትላንቱ ውጤት በኋላ በደቡብ ፈረንሳይ ሞንፔሊዬ ከተማ በሞሮኮ እና በፈረንሳይ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ ህይቱን አጥቷል፡፡ ታዳጊው የሞተው በመኪና ተገኝቶ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በፈረንሳይ እና በሞሮኮ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በመሀል ከተማዋ ላይ ለአጭር ጊዜ የቆየ ሲሆን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ለማርገብ ሞክሯል። ሞሮኮን ለ40 ዓመታት ያህል በቅኝ ግዛት ፈረንሳይ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጋ የሞሮኮ ማህበረሰብ አላት።

ሞሮኮ በካታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ላይ ስትደርስ፣ በፊፋ የዓለም የደረጃዎች ሰንጠረዥ መሪነት ላይ የሚገኙትን ቤልጂየምን፣ ስፔንን እና ፖርቱጋልን እያስወገደች በመጓዝ ነው፡፡

ይህም የአፍሪካ ቡድኖች በራስ መተማመን እንደሌላቸው፣ ረዥም ርቀትን መጓዝ አንችልም ብለው እንደሚያስቡ እንዲሁም ስነምግባር እንደሚጎድላቸው ሲቀርብባቸው የነበረውን ትችት የሚሰብር እንደሆነ የስፖርት ተንታኞች ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በውድድሩ ዝቅተኛ ግምት ለሚሰጣቸው ሀገራት የይቻላል መንፈስን የሚፈጥር እንደሆነ ነው የሚገልጹት፡፡

የዓለም ዋንጫን አልማ የተጓዘችው ሞሮኮ፣ የዋንጫው ህልሟ ባይሳካም ቅዳሜ ዕለት ከክሮሺያ ጋር ለደረጃ ትጫወታለች፡፡

ዕሁድ ዕለት ደግሞ ፈረንሳይ ከአርጄንቲና፣ የፒኤስጂዎቹ አጥቂዎች ምባፔ ከሜሲ ለዋንጫው ይፋለማሉ፡፡

የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ ፈረንሳይ፣ ለተከታታይ ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የ1962ቱን የብራዚል ታሪክ ለመጋራት ስትጫወት፣ አርጄንቲናም ለ3ኛ ዋንጫዋ ትፋለማለች፡፡ የ7 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው ሜሲ ደግሞ፣ በእግር ኳስ ህይወቱ ያላሳካውን ብቸኛውን እና ትልቁን ክብር ለማሳካት የእሁዱን ጨዋታ ይጠብቃል፡፡

XS
SM
MD
LG