በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐለም ዋንጫ ግጥሚያ ዘገባ ላይ ህይወቱ ያለፈው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ግራንት ዎል አሟሟት ይፋ ተደረገ


የስፖርት ጋዜጠኛው ግራንት ዋህል መታሰቢያ በአለም ዋንጫ 2022
የስፖርት ጋዜጠኛው ግራንት ዋህል መታሰቢያ በአለም ዋንጫ 2022

ባለፈው ሳምንት ካታር ላይ እየተካሄደ ያለውን የዐለም ዋንጫ ግጥሚያ በመዘገብ ላይ ሳለ ህይወቱ ያለፈው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ግራንት ዎል ለህልፈቱ ምክንያት የሆነው ደም ከልብ ወደተቀረው የሰውነት ክፍል የሚወስደው ትልቁ የደም ቧምቧ (ኤዮርታ) ላይ ከሚፈጠር እብጠት (ኤዮርቲክ አኒዩሪዝም) ጋር የተያያዘ መሆኑን ባለቤቱ ተናገሩ፡፡

በ49 ዐመቱ ህይወቱ ያለፈውን ጋዜጠኛ የህልፈት ምክንያት የኒው ዮርክ ከተማ የአስከሬን ምርመራ ቢሮ ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን ባለቤቱ ዶክተር ሴሊን ጉንደር ገልጸዋል፡፡

የባለቤታቸው ህልፈት ከኮቪድ አስራ ዘጠኝም ይሁን ከክትባቱ ጋር ወይም ከሌላ የተንኮል አድራጎት ጋር የተያያዘ ምክንያት እንደሌለውም አክለው አብራርተዋል፡፡

ግራንት ዎል የእግር ኳስ ጨዋታ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንዲለመድ እና እንዲወደድ ባደረገው ትልቅ አስተዋጽዖ እና ትላልቅ የስፖርት ዘገባዎችን በማቅረብ የሚታወቅ ጋዜጠኛ ነበር፡፡

ከሃያ ዐመታት በላይ “ስፖርት ኢለስትሬትድ” በተባለው መጽሄት ዘገባዎች ሲያቀርብ ከቆየ በኋላ የራሱን የስፖርት ዘገባ ዌብሳይት ከፍቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

አሜሪካውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች እና ሌሎችም ታዋቂ የስፖርት ሰዎች በጋዜጠኛ ግራንት ዎል ሞት ሀዘናቸውን እና ያላቸውን አክብሮት እየገለጹ ነው፡፡

የጋዜጠኛው አስከሬን በዚህ ሳምንት ከካታር ዩናይትድ ስቴትስ ገብቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን “ግራንት የዚህን ውብ ስፖርት ምንነት ብቻ ሳይሆን ዙሪያውን ያለውን ድባብ ግሩም አድርጎ በሚያሳይበት አዘጋገቡ እጅግ የማደንቀው ጋዜጠኛ ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG