"የኦሞ ሸለቆ የብዛሐ ህይወት እና የማኅበረሰብ ማጎልበቻ" በሚል ስያሜ የተወጠነው አዲስ ፕሮጄክት የተከፈተው በዩናይትድ ስቴትስ የዐለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤድ) አማካይነት መሆኑ ታውቋል።
ፕሮጄክቱ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በታችኛው የኦሞ ዞን ብዛሃ ህይወት ለማስፋፋት እና የማኅበረሰቡን የኑሮ መተዳደሪያ ለማሳደግ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶችን ከበሬታን ለማሻሻል እንደሚሰራ ተመልክቷል።
ስራው ከአካባቢው አስተዳደር እና በኦሞ ብሄራዊ ፓርክ እና ማጎ ብሄራዊ ፓርክ መካከል ከሚኖረው ማኅበረሰብ ጋር በአጋርነት እንደሚከናወን የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ያወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ማኅበረሰቡን መሰረት በማድረግ የተፈጥሮ አካባቢእንክብካቤን ቱሪዝምን እና የእንስሳት ሀብት ምርትን በማሳደግ ብሎም እንዲሁም የፖለቲካዊ ተሳትፎ ስልጠናዎችን በመስጠት እንደሚከናወን መግለጫው አመልክቷል።