በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደቡብ አፍሪካው የመድኃኒት ኩባኒያ  አስፐን ፋርማኬር  የ30 ሚሊዮን ዶላር  ድጋፍ አገኘ


ፋይል - የደቡብ አፍሪካው የመድኃኒት አምራች ኩባኒያ አስፐን ሠራተኛ በክትባት ክፍል ውስጥ ሲሠራ/ ኅዳር/ 2014 ዓ.ም
ፋይል - የደቡብ አፍሪካው የመድኃኒት አምራች ኩባኒያ አስፐን ሠራተኛ በክትባት ክፍል ውስጥ ሲሠራ/ ኅዳር/ 2014 ዓ.ም

የደቡብ አፍሪካው የመድሃኒት አምራች ኩባኒያ አስፐን ፋርማኬር ከጌትስ ፋውንዴሽን እና የወረርሽኞች ዝግጁነት ፈጠራዎች ጥምረት ከተባለው ተቋም የ30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።

አስፐን ፋርማኬር ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ገንዘቡ ለአፍሪካውያን በርካሽ ዋጋ የሚቀርቡ ክትባቶችን ለማምረት ይውላል።

ሙሉ በሙሉ ወደመቆም የተቃረበውን የኮቪድ አስራ ዘጠኝ ክትባት ማምረቻ ሥራ ላይ የሚያውልበትን መንገድ ሲፈልግ የቆየው አስፐን ፋርማኬር ባለፈው ሃሴው ወር ከህንዱ የመድሃኒት አምራች ኩባኒያ ከሴረም ፋውንዴሽን ጋር ስምምነት ተፈራርሟል። በስምምነቱ መሰረት አስፐን ለአፍሪካ ሀገሮች በራሱ ስም የሚወጡ አራት ክትባቶችን እንደሚያመርት አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካው አስፐን ከሴረም ኢንስቲቱት ጋር የደረሰው ይህ ለአስር ዐመት የሚዘልቅ ውል ከጌትስ ፋውንዴሽን እና የወረርሽኞች ዝግጁነት ፈጠራዎች ተቋም በሚያገኘው የገንዘብ ዕርዳታ እንደሚደገፍ አመልክቷል። ጌትስ ፋውንዴሽን እና የወረርሽኞች ዝግጁነቱ ተቋም እያንዳንዳቸው 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጡ ታውቋል።

አስፐን ከህንዱ የመድሃኒት ኩባኒያ ሴረም ጋር ባደረገው ስምምነት አፍሪካ ውስጥ በብዛት ሥራ ላይ የሚውሉ አራት ክትባቶችን አምርቶ ለማቅረብ እንደሚችል ተጠቁሟል።

የደቡብ አፍሪካው የመድሃኒት ኩባኒያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስቴፈን ሳአድ ከህንዱ "ሴረም" ጋር የተደረሰው ስምምነት ኩባኒያቸው ምን ያህል ክትባቶች እንደሚያመርት በማያሻማ መልኩ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል። አስከትለውም ኩባኒያቸው የኮቪድ 19 ክትባት ለማምረት ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ጋር ካደረገው ስምምነት በተያያዘ የምንጠብቀውን የገቢ ጉድለት ለማሟላት ያግዘናል ብለዋል ።

XS
SM
MD
LG