ኢራን ከሀገር አቀፉ የተቃውሞ ሰልፍ ጋራ በተያያዘ ባሰረችው ሁለተኛ ሰው ላይ የስቅላት ቅጣት መፈጸሟን ተከትሎ ከዓለም ዙሪያ ውግዘቱ ቀጥሏል።
ሚዛን የተባለው የኢራን ፍርድ ቤቶች የዜና አውታር በትናንት ዘገባው " ማጂድሬዛ ራናቫርድ ለሌሎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ማሻድ ከተማ ውስጥ በአደባባይ የግንባታ ሥራ መሰላል (ክሬን) ላይ ስቅላት ተፈጽሞበታል" ሲል አስታውቋል።
ራህናቫርድ የኢራን ባለሥልጣናት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በመግደላቸው ተቆጥቶ ባለፈው ወር ማሻድ ከተማ ውስጥ ሁለት የጸጥታ አባላትን በስለት ወግቶ ገድሏል ተብሎ እንደተወነጀለ ተገልጿል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በእስረኛው ላይ የተፈጸመውን የስቅላት ቅጣት አውግዟል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮም ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገልጾ የሌሎቹም የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ተቃዋሚዎች ጉዳይ እንደሚያሰጋው አመልክቷል።
ኢራን ከተቃውሞ ሰልፎቹ በተያያዘ ባለፈው ሳምንት የመጀመሪያውን የሞት ቅጣት መፈጸሟ ይታወሳል። ኢራን 12 በሚሆኑ ሰዎች ላይ በዝግ ችሎት የሞት ቅጣት ውሳኔ ማስተላለፏን ሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ተሟጋቾች ተናግረዋል። ወደሶስት ወር በተጠጋው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ቢያንስ 488 ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።
ኢራን ውስጥ የሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች ታጋዮች የተባለውና የተቃውሞ ሰልፎቹን ሲከታተል የቆየው ቡድን ቢያንስ 18 ሺህ 200 ሰዎች መታሰራቸውን ገልጿል።