በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩኤን ኤች ሲአር በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም መመለሱን ተከትሎ የሚሰጠውን ድጋፍ መጨመሩን አስታወቀ


ዩኤን ኤች ሲአር በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም መመለሱን ተከትሎ የሚሰጠውን ድጋፍ መጨመሩን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:09 0:00

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል ከስድስት ሳምንት በፊት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በግጭት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው የሰብዓዊ ድጋፍ ማጠናከር መቻሉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (ዩኤን ኤች ሲአር) አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ዩኤን ኤች ሲአር ተወካይ ዶ/ር ማማዱ ዲያን አርብ እለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ርዳታ እና ጥበቃ መጠን ጨምሯል ብለዋል።

"የሰላም ስምምነቱ የተፈረመው ጥቅምት 23 ነበር። ከዛን ግዜ ወዲህ ዩኤን ኤች ሲአር እና አጋሮቹ በትግራይ ብቻ ሳይሆን አማራን እና አፋርን ጨምሮ በጠቅላላው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚሰጡትን የእርዳታ፣ ጥበቃ እና ሌሎች መፍትሄዎች መጠን መጨመር ችለዋል። "


በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሃት መካከል ጥቅምት 23 በተፈረመው የሰላም ስምምነት የትግራይ ጦርነት እንዲያበቃ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን በዘላቂነት ለማቆም ተስማምተዋል። እንደ አሶስዬትድ ፕሬስ ዘገባ፣ ይህ ስምምነት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት እና መተዳደሪያ የጠፋበትን ሁለት አመታት ያቆጠረ አስከፊ ግጭት ለማቆም የመጀመሪያው ቁልፍ ርምጃ ነው።

ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ዩኤን ኤች ሲአር 2ሺህ 400 ሜትሪክ ቶን የሚመዝን መድሃኒት፣ የመጠለያ ቁሳቁስ፣ ብርድ ልብስ እና የቤት መገልገያ እቃዎች የያቁ 61 የጭነት መኪናዎችን እና 20 ሺህ ሊትርለዳጅ የጫነ ታንከር ወደ ትግራይ መላክ መቻሉን አስታውቋል።


"16ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ወደ 'አለምዋች' ማዘዋወር መቻላችን ብቻ ሳይሆን ከመንግስት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር ስምምነት ከተፈራረምን ወዲህ ወደ 7ሺህ የሚጠጉትን ማዘዋወር ችለናል። ስለዚህ መውጫ አጥተው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን መርዳት እና ህይወታቸውን እንደገና እንዲገነቡ ማድረግ ተችሏል።"

የስደተኛ ተቋሙ እንደ ማይጨው፣ አዲግራት እና አቢአዲ ባሉ ሁለተኛ ደረጃ የመስክ ቦታዎች ላይ ስራውን ቀጥሏል። በግጭቱም ወቅት ቢሆን የዩኤን ኤች ሲአር ቡድን ከመቀሌ እና ከሽሬ፣ በትግራይ ለሚኖሩ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ርዳታ ለማድረግ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ተገልጿል።


"የተወሰነ ድጋፍ ልንሰጣቸው ችለን ነበር። የመድሃኒት አቅርቦቶችን ይዘን ለመብረር አጋጣሚዎች ባገኘንባቸው ግዜዎች ሁሉ አድርሰናል፣ ግን በቂ አልነበረም። ከፍላጎቱ ጋር ተመጣጣኝ አልነበረም። እና ደግሞ አዎ ሰዎች በጣም ተሰቃይተዋል።"

አሶስዬትድ ፕሬስ በዘገባው በግጭቱ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት ዩ ኤን ኤች ሲአር ከሰሜን ኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

"ዩ ኤን ኤች ሲአር በስደተኞች ላይ ብቻ አይደለም እየሰራ ያለው። በግጭቱ ምክንያት በተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ላይም ጭምር እንሰራለን። እስካሁን ከ2 ሚሊየን በላይ ለሚጠጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በጥበቃ፣ በመጠለያ አቅርቦት እንዲሁም ቤት፣ መሬት፣ መተዳደሪያ እና ሌሎች አገልግሎቶችንም በማቅረብ መርዳት ችለናል።"


ዩኤን ኤች ሲአር ከወላጆቻቸው ለተለያዩ ህፃናት እና ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ጨምሮ ለተለያዩ ጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የምክር አገልግሎት እና ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል። ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ወደየመኖሪያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።

XS
SM
MD
LG