በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰጠው የ18 ወራት ጊዜያዊ ከለላ ተግባራዊ ሊሆን ነው


ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዋና ቢሮ/ ኤፒ
ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዋና ቢሮ/ ኤፒ


ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለ18 ወራት ከለላ እንዲያገኙ በጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው እቅድ ከሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከ50 ቀናት በፊት ይፋ ያደረገው ይህ እቅድ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ እስካሁን ሳይገለፅ ቢቆይም መስሪያ ቤቱ ትላንት በገፁ ላይ ባሰፈረው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከሰኞ ዲሴምበር 12 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር አስታውቋል።

የሃገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትሩ አሌሃንድሮ ማዮርካስ እቅዱ ይፋ በተደረገበት ወቅት “ዩናይትድ ስቴትስ፣ እየተካሄደ ያለው ግጭትና ኢትዮጵያን የተጫናትን ጊዜያዊ ሁኔታዎችን ይገነዘባል። የደኅንነት መሥሪያ ቤቱም ከለላ ለሚያስፈልጋቸውና በአሜሪካ ላሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ግዜያዊ ከለላ ለመስጠት ይፈልጋል” ማለታቸው ይታወሳል።

በጊዜያዊ ከለላ እቅዱ መሠረት እስከ ኦክቶበር 22/2022 ዩናይትድ ስቴትስ የገቡና እየኖሩ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የዚህ ለአንድ ዓመት ተኩል የሚቆይ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይፋ ተደርጓል። ይህ ማለት ከጥቅምት 10/2015 ዓ.ም በፊት አሜሪካ የገቡ ኢትዮጵያውያን የከለላው ተጠቃሚ ናቸው። ከጥቅምት 10 ወዲህ አሜሪካ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ግን የከለላው ተጠቃሚ እንደማይሆኑ በእቅዱ ላይ ሰፍሯል።

በአብዛኛውን ጊዜ ጊዜያዊ ከለላው በትምሕርት፣በስራ እንዲሁም ለጉብኝት መጥተው በጦርነት መይም በተፈጥሮ አደጋ ምክኒያት ወደ ሀገራቸው መመለስ ለሚፈሩ ሰዎች ነው። ማንኛው ሰው ከለላው የሚሰጠው ከሆነ ቪዛው ቢቃጠል እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ መቆየት ይችላል።
“በመካሄድ ላይ ባለ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም ለየት ያሉ እና ግዜያዊ ችግሮች ከሚባሉት ሦስት ሁኔታዎች በአንዱ ወይም ከአንድ በላይ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ጊዜያዊ የከለላ ፈቃድ ይሰጣል” ብሏል መግለጫው።

ኢትዮጵያ “በመካሄድ ላይ ባለ ጦርነትና ለየት ያሉ እና ግዜያዊ ችግሮች” የሚለውን ስለምታሟላ ከለላው መሰጠቱን የደህንነት መ/ቤቱ አስታውቋል።

ማዮርካስ እቅዱን ይፋ ሲያደርጉም “በግጭት፣ በሰብዓዊ ቀውስ፣ በምግብ እጥረት፣ በጎርፍ በድርቅ እና በመፈናቀል ምክንያት ወደ ሃገራቸው መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ያለው ሁኔታ እስከሚሻሻል በአሜሪካ እየሰሩ መቆየትና መሥራት ይችላሉ” ብለዋል።

መስሪያ ቤቱ በአሁን ሰዓት 26, 700 ኢትዮጵያውያን ከለላውን ለማግኘት ማመልከቻ ማስገባት እንደሚችሉ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG