በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን ፈረንሳይ ለግማሽ ፍፃሜ አልፋለች


በካታር የዓለም ዋንጫ/ የረንሳይ ቡድን
በካታር የዓለም ዋንጫ/ የረንሳይ ቡድን


- ሞሮኮ ደግሞ በታሪክ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ሆናለች

በካታሩ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ተጠባቂ ጨዋታ እንግሊዝን የገጠመችው ፈረንሳይ በ17ኛው ደቂቃ ኦሄሊያ ቹሄሜኒ ከርቀት ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ችላለች፡፡ ሆኖም ይሄው ተጫዋች 54ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ክልል ውስጥ በቡካዮ ሳካ ላይ በሰራው ጥፋት እንግሊዝ አቻ መሆን የቻለችበትን የፍጹም ቅጣት ምት አግኝታ ወደ ግብ ቀይራለች፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 12 ደቂቃ ሲቀረው ለፈረንሳይ ኦሊቪየር ዥሩ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠራት ግብ ፈረንሳይ ወደ መሪነቷ ተመልሳለች፡፡

የቶተናሙ አጥቂ ሃሪ ኬን የፈረንሳይን መሪነት በመግታት እንግሊዝ በዓለም ዋንጫው እንድትቆይ በማድረግ ታሪክ ለመሥራት እድሉን አግኝቶ ነበር፡፡ ነገርግን ባልተለመደ መልኩ የፍፁም ቅጣት ምቱን ከፍ አድርጎ በመምታት ፈረንሳይ ወደ ግማሽ ፍፃሜው እንድታልፍ ሲያደርግ የሀገሩ እንግሊዝ የዓለም ዋንጫ ህልም ደግሞ እንዲጨናገፍ አድርጓል።

የፈረንሳይ ቡድን ደጋፊዎች በካታር ዓለም ዋንጫ/ ኤኤፍፒ
የፈረንሳይ ቡድን ደጋፊዎች በካታር ዓለም ዋንጫ/ ኤኤፍፒ

ከፈረንሳይና ከእንግሊዝ ጨዋታ አስቀድሞ በተካሔደው የሞሮኮ እና የፖርቹጋል ጨዋታ፣ ሳትጠበቅ ረዥም ጉዞ በማድረግ ላይ የምትገኘው ሞሮኮ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ የደረሰች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር ሆናለች፡፡አጥቂው ዩሴፍ ኤን-ኔሲሪ በመጀመርያው አጋማሽ 42ኛ ደቂቃ ላይ የማሸነፊያውንና የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡

የሞሮኮ ቡድን አጥቂው ዩሴፍ ኤን-ኔሲሪ በመጀመርያው አጋማሽ 42ኛ ደቂቃ ላይ የማሸነፊያውን እና የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ካቆጠረ በኋላ/ ፎቶ ኤኤፍፒ
የሞሮኮ ቡድን አጥቂው ዩሴፍ ኤን-ኔሲሪ በመጀመርያው አጋማሽ 42ኛ ደቂቃ ላይ የማሸነፊያውን እና የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ካቆጠረ በኋላ/ ፎቶ ኤኤፍፒ

ሞሮኮ በባከነ ሰዓት ውስጥ አንድ ተጫዋቿን በቀይ ካርድ ብታጣም በውጤት ላይ ግን የፈጠረው ተጽዕኖ የለም፡፡

ድሉን ተከትሎ በሀገራቸውና በመላው ዓለም የሚገኙ የሞሮኮ ዜጎችና የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

በግማሽ ፍጻሜው ሞሮኮ ከ ፈረንሳይ ጋር የምትገናኝ ሲሆን አርጄንቲና ደግሞ ክሮሺያን ትገጥማለች፡፡ የፊታችን ማክሰኞና ረቡዕ የሚካሔዱትን እነዚህን ጨዋታዎች ጨምሮ የካታር 2022 የዓለም ዋንጫ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች ብቻ ይቀራሉ፡፡

XS
SM
MD
LG