በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ የነበሩ 83 የትግራይ ተወላጅ እሥረኞች በጠባቂዎች በጅምላ መገደላቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ


/ፎቶ ፋይል/ - በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ውስጥ የታጠቁ የትግራይ ተዋጊዎች እሥረኞችን እየጠበቁ /ጥቅምት 22, 2021/ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የትግራይ ተወላጆች ኅዳር 2021 በጅምላ መጨፍጨፋቸውን አዲስ ዘገባ ይፋ አድርጓል - ዋሺንግተን ፖስት
/ፎቶ ፋይል/ - በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ውስጥ የታጠቁ የትግራይ ተዋጊዎች እሥረኞችን እየጠበቁ /ጥቅምት 22, 2021/ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የትግራይ ተወላጆች ኅዳር 2021 በጅምላ መጨፍጨፋቸውን አዲስ ዘገባ ይፋ አድርጓል - ዋሺንግተን ፖስት

“በደቡብ ኢትዮጵያ ምዕራብ ዓባያ በተባለ ሥፍራ በነበረ ካምፕ ውስጥ ታሥረው ከነበሩ የትግራይ ተወላጅ ተዋጊዎች መካከል 83 የሚሆኑትን የካምፑ ጠባቂዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ባለፈው ዓመት ኅዳር ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፈዋል” ሲል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል። “ይህ ጭፍጨፋ የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ ከሁለት ዓመት ወዲህ አሰቃቂው ነው” ሲል ጋዜጣው ፅፏል።

“ከዚህ በፊት ያልተዘገበው ግድያ የተፈፀመው 2 ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ ወታደሮች ታስረው በነበሩበት ምዕራብ ዓባያ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ እ.ኤ.አ. ኅዳር 21/2021 ዓ.ም ነው” ብሏል ዋሽንግተን ፖስት።

ከ16 እስከ 18 የሚሆኑ የካምፑ ጠባቂዎች በእሥረኞቹ ላይ ተኩስ ሲከፍቱ አብዛኞቹ በአካባቢው ወደሚገኝ ጫካ ሸሽተው ሲገቡ ጠባቂዎቹም እንደተከተሏቸው ጋዜጣው “የዐይን እማኞች ናቸው” ያላቸውን ጠቅሶ አስነብቧል።

“ያመለጡ አንዳንድ እሥረኞች የአካባቢው ሰዎች እንዲረዷቸው ቢጠይቁም በተቃራኒው ግን 150 የሚሆኑ ሰዎች በጋራ በመሆን በቆንጨራ፣ በዱላና በድንጋይ አጥቅተዋቸዋል” ብሏል ሪፖርቱ።

“እማኝ ነን” ያሉት አክለውም በጋራ ጥቃት ፈፀሙ የተባሉት የአካባቢው ሰዎች “ከካምፑ የሸሹት የትግራይ ተወላጆች የጦር ምርኮኞች መሆናቸውንና የአካባቢው ተወላጅ ለሆኑ ወታደሮች ሞት ተጠያቂ ናቸው የሚል የሃሰት ወሬ ተነግሯቸው ነበር” ብለዋል ሲል ሪፖርቱ አክሏል።

“ወታደሮቹ ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በተደረገው ውጊያ ተሣታፊ አልነበሩም” ሲል ጋዜጣው ዘግቧል።

“ጥቃቱ የተፈፀመው የትግራይ ኃይሎች ወደ ዋና ከተማዪቱ አዲስ አበባ በመገስገስ ላይ በነበሩበት ወቅት እንደነበር”ና “በፍርሃት ወይም በቂም በቀል መነሳሳት የተፈፀመ ነው” ሲሉ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እስረኞች መናገራቸውን ሪፖርቱ ጨምሮ አመልክቷል።

83 የሚሆነው የትግራይ ተወላጆች አስከሬን በካምፑ አቅራቢያ በሚገኝ ቦታ በጅምላ መቀበሩን እማኞቹ መናገራቸውን የዋሽንግተን ፖስት ሪፖርት አመልክቷል።

“እንደ እንጨት አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርበው ነበር” ሲል አንድ ምሥክር መናገሩን ሪፖርቱ አመልክቷል።

ባለፈው ዕሁድ ለታተመው ሪፖርት ዋሽንግተን ፖስት ከሁለት ደርዘን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ማናገሩን፣ ከነዚህ ውስጥ እስረኞች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ ባለሥልጣናትና የሟቾቹ ዘመዶች እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።

በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በጥቅምት 2013 ዓ.ም ጦርነት መቀስቀሱ ይታወሳል። ሁለቱ ወገኖች በአሁኑ ወቅት የሰላም ስምምነት ዝርዝር አፈፃፀም ላይ በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

XS
SM
MD
LG