በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮንጎ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 270 ደረሰ


በኮንጎ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 270 ደረሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:00 0:00

የኮንጎ መንግስት የኤም23 ታጣቂዎች ሰኞ እለት አደረሱት ባለው እና የተኩስ ማቆም ስምምነቱን ባፈረሰው ጥቃት የሞቱት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ 270 መድረሱን አስታውቋል። የታጣቂ ቡድኑ ሊቀመንበር ግን የቁጥሩን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት የኮንጎ መንግስት ወታደሮቹ እና አጋሮቻቸው ከፈፀሟቸው አረመኔያዊ ድርጊቶች አቅጣጫ ለማስቀየር እየሞከረ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የኮንጎ መንግስት 270 ሰዎች መሞታቸውን ላስታወቀበት ጥቃት የኤም 23 ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን የታጣቂ ቡድኑ ሊቀመንበር ግን የቁጥሩን ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ በመክተት የኮንጎ መንግስት ወታደሮቹ እና አጋሮቻቸው ከፈፀሟቸው አረመኔያዊ ድርጊቶች አቅጣጫ ለማስቀየር እየሞከረ ነው ሲሉ ከሰዋል።

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ፓትሪክ ሙያያ ሰኞ እለት እንደተናገሩት መንግስት ከክልሉ ዋና ከተማ ጎማ 70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኪሺሼ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ለማጣራት ይፋዊ ምርመራ መክፈቱን ተናግረዋል።

የሀገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴር በኔዘርላንድ የሚገኘው ሄግ በመሄድም ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ አቃቤ ህግ በማቅረብ በኪሺሼ የተፀመው እልቂት እንዲጣራ መጠየቃቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎማ፣ የማህበራዊ ንቅናቄ አባላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሰብስበው በግጭቱ የሞቱትን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ለማሰብ የሻማ ማብራት አካሂደዋል።

'ኪሼሌ የስጋ ቤት አይደለም' እና 'ኦ ኪሺሼ፣ ኦ ኪሺሼ' የሚሉ መፈክሮችን ያነገቡት ተሳታፊዎች በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለውን እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ያፈናቀለውን፣ በኤም 23 አማፂ ቡድን፣ በሩዋንዳ እና በኮንጎ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ከነዚህ አንዷ የጎማ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ናዲያ ኛሙሺያ አንዷ ናት።

"እኛ እዚህ ያለነው የህገራችን ልጆች በአሸባሪው የኤም 23 በመገደላቸው እና የሀገራችን ፕሬዝዳንት የሶስት ቀን ብሄራዊ ሀዘን በማወጃቸው ነው። እኛ እንደ ወጣት የኮንጎ ተወላጆች ይህን ሀዘን ከጓደኞቻችን ጋር ለመጋራት እና ከህዝባችን ጋር ለማዘን ተጠራርጠን ነው የመጣነው።"

ሌላው በሻማ ማብራቱ ላይ የተገኘው የጎማ ከተማ ነዋሪ አማኒ ጆርዳን በበኩሉ ይህን ይላል፡

"ከዚህ በኃላ ይበቃል እያልን ነው። ሰልችቶናል። ጦርነት አንፈልግም ምክንያቱም እዚህ የመጣነው ለሰላም ነው፣ ኮንጎዎች ሰላም እንፈልጋለን፣ ከጎረቤታችን ጋር ሰላም መሆን እንፈልጋለን እነሱ ግን ሰላም ሊሰጡን አይፈልጉም። እዚህ የተገኘነው የኮንጎ ወጣቶች ጦርነት እንደማይፈልጉ፣ ሲበቃ ይበቃል የሚለውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለፕሬዝዳንታችን ጥሪ ለማድረግ ነው። እዚህ ያለነው ለጦርነት አይደለም። ነገር ግን ከታጣቂ ኃይሎቻችን ጋር በመሆን ጠላትን መዋጋት እንፈልጋለን።"

የኮንጎ መንግስት መጀመሪያ ላይ የኤም 23 አማፂያን እና የሩዋንዳ መከላከያ ኃይሎች በኪሺሼ 50 ሰዎችን ገድለዋል ሲል ከሶ ነበር። የሩዋንዳ መንግስት ግን ኤም23 ታጣቂዎችን እንደማይደግፍ በተደጋጋሚ አስታውቋል።

የኮንጎ መንግስት በአካባቢው የፀጥታ ችግር ምክንያት ቢያንስ 270 ሰዎች ሞተዋል ሲል ለጠቀሰው መረጃ ግን ሌላ ተጨማሪ ማረጋገጫ አልተገኘም። ሆኖም ሙያያ እንደሚሉት መረጃው የተገኘው ከአካባቢው የሲቪል ማህበረሰብ ነው።

የኤም 23 ሊቀመንበር በርትራንድ ቢሲምዋ ግን የሞቾቹ ቁጥር በጎሳ ሚሊሺያ መሪ ሆን ተብሎ የተጋነነ መሆኑን እና ማክሰኞ እለት በኪሺሼ በደረሰው ግጭት ስምንት ሰዎች ብቻ በተባራሪ ጥይት መሞታቸውን ይገልፃሉ።

ባለፈው ወር በአንጎላ የተካሄደውን ጉባኤ የተካፈሉ መሪዎች፣ የኤም 23 ተዋጊዎች የተኩስ ማቆም ስምምነቱን የማያከብሩ እና የተቆጣጠሯቸውን ከተሞች ለቀው የማይወጡ ከሆነ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ኃይል በግድ እንደሚያስወጣቸው ገልፀው ነበር።

በሰኔ ወር በተደረሰው ስምምነት መሰረት የቀጠናው የጦር አካል የሆኑ ከ900 በላይ የኬንያ ወታደሮች ወደ ምስራቅ ኮንጎ የተሰማሩ ሲሆን ደቡብ ሱዳንም 750 ወታደሮቿን እንደምትልክ አስታውቃለች። ከኡጋንዳ ሁለት፣ ከቡሩንዲ ሁለት የሻለቃ ቡድኖችም ጦሩን እንደሚቀላቀሉ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG