ምዕራባውያኑ ኃያላን አገሮች ሩሲያ በጎረቤቷ ዩክሬን ላይ እያካሄደች ያለውን ጦርነት “አረመኔያዊ” ሲሉ ፈርጅውታል። ክሬምሊን እጅግ በቀዘቀዘው ክረምት ውስጥ ወሳኝ በሆኑ የዩክሬን መሠረተ ልማቶች ላይ የምታካሂደውን ጥቃት መጨመሯን ተከትሎም ምዕራባውያኑ ምላሹን ሩሲያ ወደ ውጭ በምትልከው ነዳጅ ላይ ለማሳረፍ እየሞከሩ ነው። ሞስኮ ግን ሙከራዎቹን አልተቀበለችውም፡፡
ሩሲያ ሌሊቱን ባወረደችው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ኬኸርሰን ነዳለች፡፡ ቀደም ሲል በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበረችው በዚህች ደቡባዊት የዩክሬን ከተማ፣ ከሳምንታት በፊት የዩክሬን ጦር መልሶ ከተቆጣጠረ ወዲህ ጥቃቱ በርትቷል፡፡ የኬኸርሰን ነዋሪዎች ከዜሮ በታች እየወረደ ባለው ቅዝቃዜ ያለመብራት፣ ያለ ሙቀት እና የውሃ አገልግሎት እየታገሉ ሲሆን የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙት ተንቀሳቅሽ ከሆኑ ድንኳኖች ነው፡፡
ምዕራባውያን አገሮች የሩሲያን ፕሬዚዳንት ፑቲንን በዩክሬን ስለሚከተሉት ስልት እያወገዟቸው ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን ፤ “እሳቸው ክረምትን እንደመሳሪያ ሊጠቀሙበት እየሞከሩ ነው፡፡መብራት ማጥፋት፡፡ ማሞቂያዎችን ማጥፋት፡፡ ዩክሬናውያን ልክ ወደ ክረምት ወራት ሲያመሩ በጨለማ እና በቅዝቃዜው እንዲዋጡ ማድረግ ይህ በርግጥ አረመኔነት ነው፡፡" ብለዋል።
በቅርቡ በኢንዶኔዥያ በተደረገው የበለጸጉ የቡድን 20 አባል አገሮች ጉባኤ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ አንድ ላይ በመሆን ሩሲያ በዩክሬን የምታካሄደውን ጦርነት አረመኔያዊ ሲሉ የገለጹት ሲሆን እንዲቆምም ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ ስብሰባ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ “ከእውነታው ውጭ የሆነ ጥያቄዎችን በማንሳት ጦርነቱን እንዳይቆም አድርጋለች” ሲሉ ዩክሬንን ወቅሰዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑ የቡድን ሰባት አገሮች እና አውስትራሊያ አንድ ላይ በመሆን ክሬምሊን ከዩክሬን እንድትወጣ አዲስ ጫና ለመፍጠር የሩሲያ ነዳጅ በበርሜል ከ60 ዶላሮች በላይ እንዳይሸጥ ገደብ እንዲጣል ጠይቀዋል፡፡ የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክዛንደር ኖቫክ “ሩሲያ የነዳጅ ዘይቱን ምርት የምትቀንስ እንኳ ቢሆን ምዕራባውያን ባስቀመጡት የዋጋ ተመን አትሸጥም” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም በስድስት ሃገሮች ውስጥ የሚገኙ የዩክሬን ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች ባላፈው ሳምንት ውስጥ የእንስሳት ዐይን ያለበት ደም የነካቸው የደብዳቤ እሽጎች የደረሷቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ ማድሪድ ወደሚገኝ የዩክሬን ኤምባሲ የተላከ የደብዳቤ ሲከፈት በመፈንዳቱ አንድ የኤምባሲውን ሠራተኛ ማቁሰሉ ተመልክቷል፡፡ /ሙሉውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/