በቻይና ከፍተኛ ተቃውሞን አስከትሎ የነበረው የኮቪድ እገዳ በተወሰኑ ከተሞች በመጠኑ እየላላ ነው።
ባለስልጣናት እንደ ሸንጀን እና ቤጂንግ ባሉ ከተሞች ሰዎች የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ከተውሳኩ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ማሳየት አለባቸው የሚለውን ህግ አንስተዋል።
ሆኖም ግን የተውሳኩ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነው ተብሏል።
ሕጉ እንዲላላ የተወሰነው በአገሪቱ ተጥሎ ያለው እና “ዜሮ ኮቪድ” ብለው የሚጠሩት ፖሊሲ በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ በገጠመው ወቅት ነው።
ከመዲናዋ ቤጂንግ በተጨማሪ፣ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል በምትገኘውና የቴክኖሎጂ እና የማምረቻ ማዕከል የሆነችው ሸንጀን ከተማም በሕዝብ መጓጓዣ ለመጠቀም ወይም ወደ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ለመግባት ነዋሪዎች ከቫይረሱ ነጻ መሆንን የሚያሳይ ወረቀት ማሳየት አለባቸው የሚለውን ግዴታ አንስተዋል።
በቤጂንግ ግን አሁንም የመገበያያ ሱቆችና ምግብ ቤቶች ለመግባት በ48 ሰዓታት ውስጥ የተወሰደ የምርመራ ውጤት ያስፈልጋል።
ሕጉ በመጠኑ ቢላላም የተውሳኩ ስርጭት ፈጣንና ከፍተኛ ነው በሚል የዚሮ ኮቪድ ፖሊሲ የሆነውና የተያዙ ሰዎችን ሁሉ ተገልለው እንዲቆዩ የሚያዘው ደንብ አሁንም እንደሚሰራ ባለስልጣናት ተናግረዋል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 33 ሺህ 18 ሰዎች በተውሳኩ መያዛቸውን የመንግስት ሪፖርት ያሳያል።