በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከእርቅ በኋላ አፈና እና ዘረፋ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ቀጥሏል


ፎቶ ፋይል፡ በዚህ ከቪዲዮ ላይ የተወሰደው ምስል የሚያሳየው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ውስጥ በአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 14፣ 2022 የአየር ድብደባ የተደረገበት አካባቢ የህክምና ባለሞያዎች ተገኝተው ይታያል።
ፎቶ ፋይል፡ በዚህ ከቪዲዮ ላይ የተወሰደው ምስል የሚያሳየው በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ውስጥ በአውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 14፣ 2022 የአየር ድብደባ የተደረገበት አካባቢ የህክምና ባለሞያዎች ተገኝተው ይታያል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጦር አጋሮች በትግራይ ክልል ውስጥ ንብረት እየዘረፉና የጅምላ እስራት እየፈፀሙ መሆኑን የዐይን እማኞችና የእርዳታ ሠራተኞች እንደነገሩት ጠቅሶ አሶሼትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘግቧል።

ከአምስት ሚሊየን ሰዎች በላይ በሚኖሩበት ክልል የደረሰውን ስቃይ ያስቆማል ሲሉ ዲፕሎማቶች ተስፋ የጣሉበትን የሰላም ስምምነት ተፋላሚ ቡድኖቹ ከተፈራረሙ ከሦስት ሳምንታት በኃላ እነዚህ ድርጊቶች ተፈፅመዋል የሚለው ክስ አዲስ ስጋት መፍጠሩን ኤፒ በዘገባው አመልክቷል።

ጥቅምት 23፤ 2015 ዓ.ም ተኩስ የማቆም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ከተፈረመ በኃላ የእርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ መግባት ቢቀጥልም፣ አብዛኛው የትግራይ ክፍል ከተቀረው ኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት አሁንም እንደተቋረጠ መሆኑን የገለፀው ኤፒ፣ የኢትዮጵያ ኃይሎች ክልሉን እየተቆጣጠሩ ባለበት ወቅት የሰብዓዊ መብት ተመራማሪዎች ወደ ክልሉ ለመግባት አለመቻላቸው ወይም ገደብ መኖሩ ለጋዜጠኞችም ሆነ ለሌሎች ከትግራይ መረጃ ማግኘት አዳጋች እንዳደረገው ገልጿል።

ኤፒ በዘገባው የኤርትራ ወታደሮች እና ከአጎራባች የአማራ ክልል የተውጣጡ እና በትግራዩ ጦርነት ከኢትዮጵያ ፌደራል ሰራዊት ጋር ጎን ለጎን የተፋለሙ ኃይሎች፣ ባለፈው ወር በሰሜን ምዕራብ የትግራይ ኃይሎችን አስለቅቀው በተቆጣጠሩት ሽሬ ከተማ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶችን፣ የግል ንብረቶችን፣ ተሽከርካሪዎች እና የጤና ክሊኒኮችን መዝረፋቸውን ሁለት ለደህንነታቸው ሲሉ ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የእርዳታ ሠራተኞች እንደነገሩት ጠቅሷል።

በሽሬ የሚኖሩ በርካታ ወጣቶች በኤርትራ ወታደሮች መታገታቸውን የእርዳታ ሠራተኞቹ መናገራቸውንም ገልጿል። በርካታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተጠለሉባት ሽሬ በተያዘች በኋላ "ከ300 በላይ ወጣቶች" የኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች ባካሄዱት በርካታ ከበባዎች በጅምላ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ማየቱን አንደኛው የእርዳታ ሠራተኛ መናገሩን ኤፒ አመልክቷል።

"በከተማው ዙሪያ የተለያዩ እስርቤቶች አሉ" ሲል የእርዳታ ሠራተኛው መናገሩን የዘገበው ኤፒ፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌደራል ወታደሮች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ካካሄደው ህወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን ሰዎች ማሰራቸውንም ጠቅሷል ብሏል።

የትግራይ ኃይሎችን በመርዳት የተጠረጠሩ ንፁሀን ዜጎች በደቡባዊው አላማጣ ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኙና የአማራ ኃይሎች በርካታ ጓደኞቹን እንዳሰሩበት አንድ የከተማው ነዋሪ እንደነገሩትም ኤፒ በዘገባው አመልክቷል። አንድ የቀድሞ የክልሉ ባለስልጣን ከአላማጣ ከተማ በስተሰሜን 20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኮረም ከተማ እና በአካባቢው ገጠራማ አካባቢዎችም የአማራ ታጣቂዎች "የጅምላ እስር" እያካሄዱ መሆናቸውን እንደነገሩትም ገልጿል።

ኤፒ ያናገራቸው የአላማጣ ነዋሪውም ሆነ የቀድሞ የክልልሉ ባለስልጣን ለደህንነታቸው እና ሊደርስባቸው የሚችል ጥቃትን በመፍራት ማንነታቸው እንዳይጠቀስ መጠየቃቸውን አመልክቷል።

እንደ ኤፒ ዘገባ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ አለመውጣታቸው እየተካሄደ ባለው የሰላም ሂደት አሳሳቢ ጉዳይ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ከአካባቢው ለቀው እንዲወጡ ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ቃል አቀባይ እና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ አለመስጠታቸውን እንዲሁም ኢትዮጵያ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲም እንዲሁ ምላሽ አለመስጠቱን ኤፒ ገልጿል።

ከትግራይ ጋር ድምበር የምትጋራው ኤርትራ በተኩስ አቁም ስምምነቱ ውስጥ አልተጠቀሰችም። ኤፒ በዘገባው በተኩስ አቁም ድርድሩ ላይ ኤርትራ አለመሳተፏ፣ የትግራይ ባለስልጣናትን እንደስጋት የሚቆጥረው አፋኝ መንግስት ስምምነቱን ያከብራል ወይ የሚል ጥያቄ አስነስቷል ብሏል።

የጦር አዛዦቹ በኬንያ የተፈራረሙት ቀጣይ የስምምነቱ ትግበራ የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን እንደሚፈቱና ጎን ለጎንም የውጭ እና ፌደራላዊ ያልሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንደሚወጡ ያስቀምጣል።

ሆኖም የእርዳታ ባለስልጣናት፣ ዲፕሎማቶችና ሌሎች በትግራይ የሚገኙ አካላት የኤርትራ ኃይሎች አሁንም በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን እና ይህ የሰላም ስምምነቱን እንደሚጎዳ መናገራቸውን የኤፒ ዘገባ ያመለክታል። የኤርትራ ወታደሮች የቡድን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በግጭቱ ከደረሱ አሰቃቂ ጥቃቶች አንዳንዶቹን መፈፀማቸው ክስ ይቀርብባቸዋል።

በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ መቀመጫውን ያደረገው የትግራይ ቴሌቭዥን ኅዳር 10 ቀን ባስተላለፈው ዘገባ የኤርትራ ወታደሮች በመካከለኛው ትግራይ በሚገኝ ኢግላ በተሰኘ አካባቢ 10 ህፃናትን ጨምሮ 63 ንፁሃን ዜጎችን መግደላቸውን እንደዘገበ የጠቀሰው የኤፒ ዘገባ፣ የቴሌቭዥን ዘገባው የጠቀሳቸው የዓይን እማኞች ነዋሪዎች የሞቱባቸውን ሰዎች እንዳይቀብሩ እንደተከለከሉ መናገራቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ሰኞ እለት ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ "የውጭ ኃይሎች መውጣት እና የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታትን" ጨምሮ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የሚንስትር መስሪያቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።

ህዳር 8 ቀን 2025 ዓ.ም በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ አክሱም ከተማ አራት ወጣቶች በኤርትራ ኃይሎች መገደላቸውን የእርዳታ ሰራተኛ እንደነገሩት ኤፒ ገልጿል። የእርዳታ ሰራተኛው "የሰላም ስምምነት ቢኖርም ግድያዎቹ ግን አላቆሙም። በአክሱም በኤርትራ ኃይሎች ብቻ እየተፈፀመ ነው።" ማለታቸውንም ጠቅሶ ዘግቧል።

የትግራይ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የኤርትራ ጦር "በትግራይ ውስጥ አሰቃቂ ግፍ እየፈፀመ ነው" ማለቱን የጠቀሰው የኤፒ ዘገባ፣ መግለጫው የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከስምምነቱ በኃላ "ወታደሮቹን እንዲያስወጣ ቢጠበቅም፣ ተጨማሪ ኃይሎችን ወደትግራይ እያስገባ ነው" ሲል መክሰሱንም አመልክቷል።

ባለፈው አመት የትግራይ ኃይሎች ወደ ፌደራል ዋና መቀመጫ ለመግፋት ባደረጉት ጥረት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው አስከፊ ጦርነት ለወራት ተቋርጦ ከቆየ በኃላ እንደገባ በነሐሴ ወር አገርሽቶ ነበር።

ትግራይ ለሁለት ዓመታት በተጣለባት የእርዳታ ገደብ ምክንያት አሳሳቢ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች ያለው የኤፒ ዘገባ እነዚህ ገደቦች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎች ፓናል ምናልባት የኢትዮጵያ መንግስት "ረሃብን እንደጦር መሳሪያ" ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አላማቸው የክልሉን አማፂ መሪዎች መያዝ መሆኑን በመግለፅ በትግራይ የሚኖሩ ንፁሃን ዜጎችን ኢላማ በማድረግ የሚቀርብባቸውን ክስ እንደማይቀበሉትም አመልክቷል።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም አሁንም እንደ ስልክ፣ መብራት እና የባንክ አገልግሎቶች በአብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች ዝግ ናቸው። ዩናይትድ ስቴትስ በሁለቱም ወገኖች ጥቃት በተፈፀመበት ጦርነት በመቶ ሺዎች የሞቆጠሩ ሰዎች ተገለው ሊሆን እንደሚችል ግምት አስቀምጣለች።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ የፌደራል ባለስልጣናት ወደ ትግራይ "ያልተገደበ ሰብዓዊ አቀርቦት" እንዲያመቻቹ ይጠይቃል። የዓለም ምግብ ፕሮግራም አርብ እለት ባወጣው መግለጫ ከስምምነቱ ወዲህ 96 ምገብ እና ነዳጅ የጫኑ መኪናዎችን መላኩን ቢገልፅም ወደ መካከለኛው እና ምስራቅ ትግራይ ያለው ተደራሽነት አሁንም የተገደበ መሆኑን የኤፒ ዘገባ ያመለክታል።

ኤፒ በዘገባው በርካታ ቁጥር ያላቸው የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል እየገቡ ቢሆንም አሁንም ብዙ ክልከላዎች በመኖራቸው ያልተገደበ አቅርቦት እስካሁን እንዳልተረጋገጠ አንድ የእርዳታ ሰራተኛ አርብ እለት እንደነገሩት ገልጿል። የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ወደ ትግራይ የሚወስዱት የገንዘብ መጠን ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን የፍተሻ ኬላ እና ወታደራዊ አዛዦች የእርዳታ ሰራተኞች በክልሉ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንደሚያስተጓጉሉ የእርዳታ ሰራተኛው መናገራቸውን የኤፒ ዘገባ ጨምሮ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG