በውዝግቦች የተሞላው 22ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ 3 ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ያላት ኳታር፣ ለ12 ዓመታት ሲቀርብባት የዘለቁ ትችቶችን እና ነቀፌታዎችን ተቋቁማ ውድድሩን በከፍተኛ ድምቀት አስጀምራለች፡፡
በተለያዩ ዝግጅቶች የተከናወነው የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ፣ ሰባት ትዕይንቶችን ያስተናገደ ሲሆን፣ እነዚሁም አዘጋጆቹ እንዳሉት "ዓለም አቀፍ የጥበባት ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች የተሳተፉበት እና በታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያዎች ታጅቦ የኳታርን ባህል ከአለምአቀፍ ባህል ጋር በማጣመር” የተዘጋጁ ናቸው።
ከባህላዊ የአረብ ሙዚቃዎች እስከ ዘመናዊ ዳንሶች ኳታር ባህሏን ከዓለም አቀፍ ሙዚቃዊ ጣዕም ጋር አዳምራ፣ በተዋበ ድባብ ኦፊሴላዊ የዓለም ዋንጫ ዜማዎችንም በማካተት ለዓለም እንካችሁ ብላለች፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ ዳንሰኞች እና ሙዚቀኞች ወደ መድረክ እየወጡ ባሉበት ወቅት የሆሊውዱ ኮከብ ሞርጋን ፍሪማን ባደረገው ንግግር የተስፋ፣ የአንድነት እና የመቻቻል መልእክት አስተላልፏል።
"እግር ኳስ ሀገራትን አንድ ያደርጋል” ያለው ፍሪማን፣ “ሀገራትን የሚያገናኘው እግር ኳስ ማህበረሰቦችንም አንድ ያደርጋል" ሲልም አክሏል።
እናም በእነዚህ መለያየት በበዛባቸው ጊዜያት ዓለም አንድ ላይ የምትሰበሰብበት ጊዜ ነው ሲል በአጽንኦት ተናግሯል፤ 60 ሺህ ተመለክቾችን በሚያስተናግደው አል ባይት ስታዲየም ከተሰየሙ ደጋፊዎችም አድናቆትን ቸረውታል፡፡
የኳታር ንጉስ (ኤሚር)ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ በመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በውድድሩ ለመታደም ከመላው ዓለም ወደ ሀገራቸው የተመሙትን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡
"ሰዎች ልዩነታቸውን ለማክበር የሚከፋፍሏቸውን ወደ ጎን ቢተዉ እንዴት ውብ ነው" ብለዋል፣ ከስደተኛ ሰራተኞች ኢሰብዓዊ አያያዝ እና የአልኮል መጠጥን ጨምሮ ሌሎችም ክልከላዎች ጋር በተያያዘ ትችትን ሲያስተነናግዱ የከረሙት የኳታሩ መሪ፡፡
የዓለም ዋንጫ ውድድር በመልካም እና የተስፋ ቀናት የተሞላ ይሆን ዘንድ ምኞታቸውንም በመግለጽ፣ ለዝግጅቱ ሀገራቸው 200 ቢሊዮን ዶላር አውጥታበታለች ተብሎ የታመነውን በታሪክ ውውን የዓለም ዋንጫ ውድድር አስጀምረዋል፡፡
የመክፈቻ ስነስርዓቱ ከስታዲየሙ በላይ ያለውን ሰማይ ልዩ ውበት ባጎናጸፉት የርችቶች ተኩስ ተጠናቋል፡፡
ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ደግሞ አስተናጋጇ ኳታር ከኢኳዶር ጋር የውድድሩን የመክፈቻ ጨዋታ በማድረግ ላይ ስትሆን፣ የመጀመሪያውን 45 ደቂቃ ኢኳዶር 2 ለ 0 እየመታች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ በኢኳዶር ፍጹም የበላይነት እየተካሔደ ባለው በዚህ ጨዋታ፣ ሁለቱንም የጨዋታውን ግቦች ከፍተኛ ተጽእኖ በመፍጠር ላይ የሚገኘው ኤነር ቫሌንሲያ አስቆጥሯል፡፡ እነዚሁ ጎሎች የ22ኛው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ግቦችም ናቸው፡፡
/ፎቶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ/