በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ ለ2023 የመከላከያ ወጭዋ 13 ቢሊዮን ዶላር ሰበሰበች


በደቡባዊ ዩክሬን ከኼርሰን ግዛት ከወደመው ትምህርት ቤት ዳር የወዳደቁ የጥይት ሳጥኖች እኤአ ህዳር 16/ 2022
በደቡባዊ ዩክሬን ከኼርሰን ግዛት ከወደመው ትምህርት ቤት ዳር የወዳደቁ የጥይት ሳጥኖች እኤአ ህዳር 16/ 2022

ሩሲያ እኤአ የ2023 የመከላከያ ወጭዋን ለማሳደግ በአንድ ቀን ውስጥ እስከዛሬ ትልቁ ነው የተባለውን ዋስትና በመስጠት የ13.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር መሰብሰቧን የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር ባላፈው ረቡዕ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መረጃ በመንግሥት የተሰጠው የብድር ዋስትና የዩክሬኑ ወረራ ከተጀመረ ወዲህ እየጨመረ የመጣውን ወታደራዊ ወጭ ለማስቀጠል ቁልፍ ዘዴ ነው ብሏል፡፡

ሩሲያ እኤአ ለ2023 ያወጣችው በጀት እኤአ በ2021 ይፋ ካደረገችው 40 ከመቶ በመጨመር 84 ቢሊዮን ዶላር መድረሱም በዘገባው ተገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና ሩሲያ በተለያዩ የዩክሬን ከተሞች በሚገኙ የኃይል አውታሮች ላይ ከፍተኛ ድብደባ ማድረሷ ተነግሯል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ትናንት አርብ በሰጡት መግለጫ በ17 የዩክሬን ክልሎችና በዋና ከተማዪቱ ኪቭ የኃይል አቅርቦቱ ችግር መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የበረታው ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች መሆኑ በተነገረበት ኪቭ የኃይል አቅርቦቱ ሙሉ ለሙሉ ሊቋረጥ እንደሚችል የዩክሬን ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል፡፡

የከተማዪቱ ከንቲባ ቪታሊ ክሊስችኮ ባለሥልጣናቱ የከተማውን ኃይል መስጫ ጣቢያ መልሶ ለማስቀጠል ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመብራት መቆራረጡ በዚሁ ከቀጠለ በዚህ ክረምት ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ሊደርስ እንደሚችል ስጋት አለኝ ብሏል፡፡

XS
SM
MD
LG