በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ተለቀቀ


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ለስድስት ወራት በእስር የቆየው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ከሰዓት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወጥቶ ከቤተሰቦቹ ጋር መቀላቀሉን ወንድሙ አቶ ታሪኩ ደሳለኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ወንጀል አንደኛ ፀረ ሽብር ችሎት ተመስገን በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ የመፈቻ ትዕዛዝ ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተልኮ የነበረ ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ ሊለቀው ፈቃደኛ አለመሆኑን ጠበቃው እና ወንድሙን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

በዚህም ምክንያት ዛሬ ጠዋት ከጠበቃው ጋር በመሆን ማረሚያ ቤቱን ለፍርድቤት መክሰሳቸውን የገለፁት ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ፍርድቤቱ በድጋሚ ለማረሚያ ቤቱ መጻፉን ገልጸዋል።

ቀደም ሲልም ይኸው ችሎት ተመስገን በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቅ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ዓቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ ሳይፈታ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ማረሚያ ቤቱ ትላንት ትዕዛዙን ያልለቀቀበትን ምክንያት የተመስገን ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ ሲናገሩ ቀደም ሲል ከፍርድ ቤት ጋር በተለዋወጧቸው የፅሁፍ ሰነዶች የሚያውቀው ጉዳዩ ‘የሽብር ጉዳይ’ የነበረ መሆኑን መጠቆሙንና ትላንት ተፅፎ የደረሰው የተለየ በመሆኑ እንደሆነ ማሳወቁን ገልፀው “’ፍርድ ቤቱን ማብራሪያ እንዲሰጠኝ በደብዳቤ እጠይቃለሁ’ ብሏል” ብለዋል፡፡

ሆኖም “’የሽብር ጉዳይ የተባለው ነገር ማረምያ ቤቱ ያመጣው አዲስ ነገር ነው” የሚሉት አቶ ቤተማርያም በፍርድ ቤትና በማረምያ ቤቱ መካከል እንዲህ ዓይነት መፃፃፍ እንዳልነበረ ተናግረዋል።

ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል አካባቢ ተመስገን ራሱ ከእስር መፈታቱን እንደደወለላቸው የሚገልፁት አቶ ታሪኩ "ከምንም ነገር በላይ ከተከሰሰባቸው አብዛኞቹ ክሶች ነፃ መባሉ እና ከእስር መውጣቱ አስደስቶናል" ብለዋል። ቀደም ብለው አስይዘውት ከነበረው የ100 ሺህ ብር ዋስትና ብር 70 ሺህ ብሩ እንዲመለስላቸው መደረጉንም አመልክተዋል።

ተመስገን በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ሞራልና ስሜት ላይ እንደሚገኝ እና በመጪዎቹ ቀናት የጤና ምርመራ እንደሚያደርግ አቶ ታሪኩ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG