በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኮንጎ ጦርና ኤም 23 ጎማ አቅራቢያ ገጠሙ


ከኤም 23 ጋር የሚፋለሙት የኮንጎ ጦር አባላት በሩትሽሩ ከተማ አቅራቢያ
ከኤም 23 ጋር የሚፋለሙት የኮንጎ ጦር አባላት በሩትሽሩ ከተማ አቅራቢያ

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር ኤም 23 ከተባሉት አማጺያን ጋር በምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል ካለችው ጎማ ከተማ በስተሰሜን ዛሬ እሁድ መጋጨታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የኮንጎ ሠራዊት የኤም 23 አማጺያንን ከጎማ 20 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሚገኝና ምዋሮ በተባለ አካባቢ ገጥመው እንደነበር ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በአብዛኛው ከቱትሲ ጎሳ የተዋቀረው ኤም 23 ሰሙኑን ኮንጎ ውስጥ በከፈተው መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰፊ ግዛቶችን ተቆጣጥሯል ተብሏል።

አማጺያኑ ትናንት ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ፣ የኮንጎ ጦር ጭካኔ የተሞላበት የአየር ድብደባ ሠዎች በብዛት በሚኖርባቸው አካባቢዎች አድርጎ 15 ሲቪሎችን ገድሏል ሲሉ ወንጅለዋል።

የኤ. ኤፍ. ፒ. ዘግባ ግን የሟቾቹን ቁጥር በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ እንዳልቻለ ጠቅሷል።

ግጭቱ የተከሰተው የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሠብ በተሰኘውና ሰባት አገራት በአባልነት የሚገኙበት ወታደራዊ ል ዑልክ ውስጥ የሚሳተፈው የኬንያ ሠራዊት ኮንጎ በገባ በማግስቱ ነው ተብሏል።

በኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል 120 የሚሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ይገኛሉ።

ኤም 23 በእ. አ. አ. 2012 ጎማን ለጥቂት ጊዜያት ተቆጣጥሮ የቆየ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ እንዲለቅ ተገዷል።

የኤም 23 እንደገና ማንሰራራት በኮንጎና፣ አማጺያኑን የረዳሉ ስትል በምትከሳት ሩዋንዳ መካከል ቅራኔ ፈጥሯል።

ኪጋሊ ውንጀላውን ብታስተባብልም፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተዘጋጀ፣ ነገር ግን ለእትመት ያልበቃ ሪፖርት ሩዋንዳን ተጠያቂ እንዳደረገና የተባለውንም ሰነድ መመልከቱን ኤ. ኤፍ. ፒ. በሪፖርቱ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG