በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ድንገተኛ ኅልፈት


ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ
ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ

ኢትዮጵያ የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ኅትመት በዐዋጅ ከፈቀደችበት የ1980ዎቹ ማግስት አንሥቶ፣ በነጻው ፕሬስ ተሳትፏቸው በጉልሕ ተጠቃሽ ከኾኑ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የኾነው ዳዊት ከበደ ወይሳ፣ ትላንት ረፋድ በዐዲስ አበባ ከተማ ሕይወቱ በድንገት አልፏል።

በዐዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ "ቄራ-ኬላ በር " ታህሣሥ 19 ቀን፣ 1961 ዓ.ም. የተወለደው ዳዊት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በካቴድራል እና በፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤቶች፤ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከታታሉን ከቅርብ ወዳጆቹ ሰምተናል።

ከተግባረ እድ የቴክኒክ እና ሞያ ትምህርት ቤት፣ በ1979 ዓ.ም. የተመረቀው ዳዊት፣ ከጥንቱም የሥነ ጽሑፍ ተውህቦ ነበረው። በ1986 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምሽት ትምህርት የቋንቋ እና የስነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ከተቀላቀለ፣ዝንባሌውን በልዩ ልዩ ሥልጠናዎች ከአጎለበተ በኃላ፣ ፈር ቀዳጅ በነበሩ የግል ጋዜጦች እና መጽሔቶች ላይ፣ ከዓምደኝነት እስከ ዋና አዘጋጅነት ለመሥራት በቅቷል።

ዳዊት፣ ፖለቲካ ነክ ጽሑፎቹን ከአቀረበባቸው የኅትመት ውጤቶች መካከል፥ "ፈለግ"፣ "ሞገድ" እና "ማዕበል" የተሰኙት ሳምንታዊ ጋዜጦች ይጠቀሳሉ። "ወይ ፍቅር" እና "ብሌን" ደግሞ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጣጥፎቹ ከታተመባቸው የወቅቱ መጽሔቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

"ፊያሜታ " የተሰኘውን የራሱን ጋዜጣ በ1988 ዓ.ም. በመመሥረት እና በዋና አዘጋጅነት በመምራት፣ ትኩረት የሳቡ ሀገራዊ ጉዳዮችን ለአንባብያን ሲያስቃኝ ቆይቷል። ዳዊት ከበደ፣ የሀገሩን ምድር የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በመልቀቅ መጀመሪያ ወደ ኬንያ በመቀጠል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በስደት ከአቀና በኋላ፣ የጋዜጠኝነት ሥራውን በተለያዩ መድረኮች ቀጥሏል።

በተለይ ከሥራ አጋሩ ክንፉ አሰፋ ጋራ "ኢትዮፎረም" በሚል ስያሜ በመሠረተው የበይነ መረብ አውታር፣ ከ10 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውንንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያንን የሚመለከቱ በርካታ ጽሑፎችንና መረጃዎችን አድርሷል። በተጨማሪም፣ "ትንሣኤ" የተሰኘ ራዲዮ ጣቢያ ዋና አዘጋጅ ፣ መቀመጫውን በአትላንታ ከተማ ያደረገው "አድማስ" ራዲዮ ተባባሪ አዘጋጅ ኾኖ አገልግሏል።

ዳዊት፣ ከሞያዊ አበርክቶው ጎን ለጎን፣ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በመደገፍ፣ የኢትዮጵያውያን መገናኛ መድረኮችን በማስተባበር ጥረቱ እና ደግነቱ በብዙ የሥራ አጋሮቹ ዘንድ በበጎ ይነሣል። ሰሞኑን ለጉብኝት ወደ ዐዲስ አበባ ያቀናው አንጋፋው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ፣ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ሕይወቱ በድንገት ማለፉ ተሰምቷል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቤተ ሰዎቹ፣ ባልንጀሮቹ እና የሥራ አጋሮቹ በተገኙበት፣ ቅዳሜ ኅዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም፣ ከአስተባባሪ ወዳጆቹ ሰምተናል።

XS
SM
MD
LG