በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት የኬንያ ውይይት


የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት የኬንያ ውይይት
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:59 0:00

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላትና እና የህወሃት ታጣቂዎች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በናይሮቢ ውይይት ጀምረዋል።

ውይይቱ የትጥቅ መፍታት ጉዳዮችን ጨምሮ የግጭት ማቆም ስምምነቱ አፈፃፀም ላይ ያተኮረ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በስብሰባው ከሚጠበቁት ውጤቶች መካከል “የጦር መሳሪያ ድምጾችን ጸጥ ማሰኘት፣ የሰብአዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማሳለጥ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ያለውን አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዱ መንገዶችን ማበጀት” እንደሚገኙበት ሕብረቱ ገልጿል፡፡

ንግግሩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ውይይቱን፣ የኢትዮጵያን “ደህንነት የሚያረጋግጥ እና እስካሁን ድረስ ተደራሽ ወዳልሆኑ አካባቢዎች ሰብአዊ ፍሰቱን የሚያፋጥን ነው” ያሉ ሲሉ፤ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ “የምናከናውነው እያንዳንዱ ተግባር፣ ወይም የምንፈርመው እያንዳንዱ ስምምነት የትግራይን ህዝብ ጥቅም የሚያረጋግጥ ነው” ብለዋል።

ቁጥራቸው የበዛ ሰዎችን ሕይወት ያሳጣውን "በዘላቂነት" ለማስቆም ባለፈው ሳምንት በተፈረመው ስምምነት መሰረት በወታደራዊ እና ሌሎች ዝርዝሮች ዙሪያ ለመወያየት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ክልል ተወካዮች መካከል አዲስ ውይይት ተጀምሯል።

በኬንያ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ በሁለቱም ወገኖች ያሉ ወታደራዊ አዛዦች እና የፖለቲካ ተደራዳሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ለውይይት ከሚቀርቡት ጉዳዮች ውስጥ ስምምነቱን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት እና በኢትዮጵያ ሰሜናዊ የትግራይ ክልል የሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽነት እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመር ይገኙበታል። ዋና አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ እነዚህን መተማመን የሚያጎለብቱ ቁልፍ እርምጃዎች በመውሰድ፣ ስምምነቱን ለማስፈጸም አሳይተዋል ላለው ቁርጠኝነት የኢትዮጵያን መንግሥትና ህወሃትን በዛሬው መግለጫው አመስግኗል።

የዛሬው ስብሰባ፣ ሁለቱ አካላት በቅርቡ በተፈራረሙት ግጭት የማቆም ስምምነት አንቀጽ 6 (መ) መሰረት የሚከናወን መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡ ይኸውም “ስምምነቱ በተፈረመ በ 5 ቀናት ውስጥ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በመሬት ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የትጥቅ መፍታት ጉዳዮችን ጨምሮ በስምምነቱ አፈፃፀም ላይ በዝርዝር ለመወያየት በተስማሙት” መሰረት የሚካሔድ እንደሆነ አብራርቷል፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ንግግሩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በዛሬው እለቱ ሁለቱ ወገኖች በውይይቱ አካሄድ ላይ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ወደ ትግራይ የሚገባው ሰብዓዊ ርዳታ በቀናት ውስጥ እንደሚጀምር ገልፀዋል።

"ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አጋማሽ የጭነት የሰብዓዊ ርዳታ የቻኑ መኪናዎች መግባት ይጀምራሉ" ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን አክለው የትግራይን ማኅበረሰው ከቀሪው የሀገሪቱ ክፍል ጋር ማገናኘት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል።

አያይዘውም "ልንደርስባቸው በማንችላቸው አካባቢዎች የስልክ፣ የኃይል እና የባንክ አገልግሎቶችን በፍጥነት ማገናኘት አለብን። ነገር ግን ከሁሉም በፊት ህዝባችን ምግብ እና መድሃኒት ይፈልጋል። ያንን ለማፋጠን እየሞከርን ነው።" ብለዋል።

የትግራይ ክልል ዋና ተደራዳሪ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ትግራይ መግባት መጀመር ለንግግሩ መተማመንን እንደሚጨምር አስረድተዋል።

"ሰዎች እዚህ በምናደርገው ነገር የበለጠ መተማመን እና የበለጠ ተስፋ ባዩ ቁጥር እኔ እና ሬድዋንን ጨምሮ እዚህ ያለነው ለወታደሮች ተኩስ ለማቆም አስቸጋሪ እንዳይሆንባቸው እናደርጋለን"

አቶ ጌታቸው አክለው የሰላም ስምምነቱ መተግበር ለሀገሪቱ ተጨማሪ እድሎችን እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

"በስምምነታችን ውስጥ የተዘረዘሩ በርካታ መፈፀም ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። የአገልግሎቶች አቅርቦትን መልሶ ማስጀመር አንዱ ነው።” ካሉ በኋላ “አገልግሎቶች በተመለሱ ቁጥር የበለጠ መተማመን ይፈጥራል። የበለጠ መግባባት ሲኖር በሰዎች አይምሮ ውስጥ የበለጠ ተስፋ ይኖራል። ያ አሁን ልናመጣው እየጣርን ያለነውን ሰላም ያጠናክራል። እኛ የገባነውን ቃል ለመፈፀም ቁርጠኛ ነን።" ብለዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የፈረሙት ስምምነት የትግራይን ህዝብ ፍላጎት የሚያስጠብቅ መሆኑን ገልፀዋል። አክለውም "የምንታገለው የውጊያ ፍላጎት ኖሮን ሳይሆን እንደ ህዝብ ህልውናችን አደጋ ላይ ስለወደቀ ነው። የሰላም ስምምነት ህልውናችንን የሚያረጋግጥልን ከሆነ ለምን አንሞክረውም?" ብለዋል።

አንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑና በይፋ አስተያየት መስጠት ባለመቻላቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለስልጣን ለአሶስዬትድ ፕሬስ እንዳስታወቁት፣ በኬንያ መንግስት አስተናጋጅነት የሚካሄደው ንግግር እስከ እሮብ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ባለስልጣኑ አክለው ሁለቱ ወገኖች "ውጊያ መቆሙን ለሁሉም ተዋጊዎቻቸው ለመግለፅ ያለውን የመስመር ችግር ስለሚገነዘቡ" ሊከሰት የሚችለውን ማንኛውንም ችግር ለመፍታት የግንኙነት መስመር መቋቋሙን ገልፀዋል።

ውይይቱን ከሚያመቻቹት እና ከሚሳተፉ መካከል የአፍሪካ ህብረት ተወካይ እና የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሌሴንጎን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የናይጄሪያ፣ የደቡብ አፍሪካ እና የኬንያ ወታደራዊ መኮንኖች ይገኙበታል። ዩናይትድ ስቴትስ እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ)ም በታዛቢነት ይገኛሉ።

"ለሚቀጥለው ስብሰባችን ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ እንደምንሄድ ተስፋ እናደርጋለን" ያሉት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኬንያታ "በመጨረሻም ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ በአንድነት ያከብራሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

​"በዚህ ሂደት ማጠቃለያ ላይ ለሀገራቸው መሻሻል፣ ለኢትዮጵያ መሻሻል፣ ለቀጠናችን ጥቅም በጋራ የሚሰሩ እና በመጨረሻም በህዝባችን ደህነንት ላይ እንድናተኩር፣ አፍሪካን የተሻለች አህጉር ለማድረግ እና ጦርነትን በዘላቂነት ለማቆም በምናደርገው ትግል አብረው የሚሰሩ ባልደረቦች ይሆናሉ። " ብለዋል።

"ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብናል" ሲሉ በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ለዲፕሎማቶች ገለፃ ያደረጉት የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ሬድዋን የገንዘብ ሚኒስቴር ሀገሪቱን እንደገና ለመገንባት 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መገመቱን አስታውቀዋል።

አምባሳደሩ አክለው "በትግራይ የስልክ እና የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአስቸኳይ እንጠግናለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አጋር ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች መሰረታዊ የህክምና አቅርቦቶች እንኳን እያለቁ መሆኑን ያሳወቁትን ጉዳይ በተመለከተ አምባሳደር ሬድዋን ሲያስረዱ "ያለብን ብቸኛው እንቅፋት የጦር አዛዦች ሁኔታውን እስኪገመግሙ ድረስ በረራዎችን ለመፍቀድ አደገኛ መሆኑ ነው" ያሉ ሲሆን የጦር አዛዦቹ በጊዜ ገድብ ላይ ከተስማሙ እና መንግስት የአየር ክልሉን እና የአየር ማረፊያውን ሙሉ ለሙሉ ከተቆጣጠረ በኃላ ትግራይ ክልል በመንገድም ሆነ በአየር ለሰብዓዊ ርዳታ ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

ወታደሮቿ ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ሆነው የተዋጉት ጎረቤት ሀገር ኤርትራ የሰላም ንግግሩ አካል አልነበረችም። ባለፈው ሳምንት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በቀጥታ ባይጠቅሳትም በሁሉም የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድምበሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲሰማራ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲያስከብር፣ እንዲሁም ከውጭ ወረራ እንዲከላከል ይደነግጋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በግጭቱ ወቅት የኢትዮጵያ ድንበሮች እና የአየር ክልል ተጥሷል ሲሉ በመግለጫቸው ያመለከቱ ሲሆን "እርስ በርስ በመፋለም እና አንዳችን አንዳችንን በማዳከን ተጠምደናል። ይህ ሶስተኛ ወገን የበለጠ እንዲያዳክመን መንገዱን ከፍቷል " ብለዋል። አክለውም ኤርትራን በስም ባይጠቅሱም፣ ለዚህ የሰላም ሂደት ፍላጎት ላይኖረው የሚችል ሶስተኛ አካል ሊኖረን ይችላል" ሲሉ ገልፀዋል። ስምምነቱን በተመለከተ እስካሁን ከኤርትራ በኩል በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡

የደቡብ አፍሪካው ስምምነት በተፈረመ በ24 ሰዓታት ውስጥ በሁለቱ አካላት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች መካከል ግንኙነት እንዲፈጠርና በሂደቱ ላይ በአምስት ቀናት ውስጥ ውይይት እንዲያደርጉ የሚደነግግ ሲሆን፣ ቀጥሎም በኮማንደሮቹ ስምምነት መሰረት፣ በ 10 ቀናት ውስጥ ለከባድ መሳርያዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት የትጥቅ ማስፈታቱ ተግባር እንዲጀመር ይላል፡፡ ትንንሽ መሳርያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የትጥቅ አፈታት ሂደቱ፣ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ሁለቱ አካላት መስማማታቸውንም ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ "የሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ትጥቅ የማስፈታቱን ዝርዝር እቅድ ሲያዘጋጁ፣ እንቅስቃሴው የጊዜ ማራዘሚያ የሚጠይቅ ከሆነ ምክረ ሐሳብ ሊሰጡ ይችላሉ" ሲሉየጊዜ ገደቡ ሊራዘም እንደሚችል አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG