የኢራቅ ህግ አውጪዎች በሀገሪቱ ወታደራዊ ግዳጅን የሚያስጀምረው ህግ ከተወገደ ከ20 ዓመት በኋላ በድጋሚ ለማስጀመር ረቂቁን በመመርመር ላይ መሆናቸውን አስታወቁ።
እ.ኤ.አ ከ1935 አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ የሚመራ ሃይል አምባገነኑን የሳዳም ሁሴን መንግስት እስካባረረበት እስከ 2003 ድረስ በኢራቅ ወታደራዊ አገልግሎት ግዳጅ ነበር።
ህጉ እድሜያቸው ከ 18 እስከ 35 ዓመት ለሆኑ ወጣት ወንዶችን እንደ የትምህርት ደረጃቸው ከ3 እስከ 18 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ለውትድርና እንዲመዘገቡ የሚያደርግ እንደሆነ የፓርላማ አባል የሆኑት ያሲር ኢካንደር ዋቱት ለኤኤፍፒ የዜና ተቋም ገልጸዋል።
የግዳጁ ተሳታፊዎችም ከ600,000 እስከ 700,000 የኢራቅ ዲናር ወይም ከ400 ዶላር በላይ የሚደርስ አበል እንደሚከፈላቸው የመከላከያ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዋቱት ገልጸዋል።
ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ተፈጻሚ ለመሆን ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሲሆን ከዚህ ግዳጅም ለቤተሰቦቻቸው ብቸኛ ልጅ የሆኑና ቤተሰብ የማስተዳደር ሃላፊነት ያለባቸው ብቻ እንደሚቀሩም ተገልጿል።