በአፍሪካ እየጨመረ የመጣው የኢቦላ ወረርሽኝ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ የዓለም የጤና ባለሙያዎች አስታውቀዋል። መስከረም አስር በኡጋንዳ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ፣ በአፍሪካ እየጨመረ የመጣው ገዳይ በሽታ የቅርብ ግዜ ክስተት ነው። እ.አ.አ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ 32 የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን እና አስራ ዘጠኙ የታዩት ባለፉት አስር አመታት ውስጥ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
በዓለም ጤና ድርጅት ትንታኔ መሰረት ኢቦላ እና ሌሎች በቫይረስ ምክንያት ደም መፍሰስ የሚያስከቱ ትኩሳቶች ከእነዚህ ወረርሽኞች 70 ከመቶ ያክሉ ናቸው። ሌሎቹ 30 ከመቶ ወረርሽኞች ደንጌ ትኩሳት፣ አንትራክስ፣ ቸነፈር አነ የዝንጀሮ በሽታን ያጠቃልላሉ።
በጤና ድርጅቱ በኡጋንዳ ለተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ የአፍሪካ ክስተት ስራ አስኪያጅ የሆኑት ፓትሪክ ኦቲም እንደሚያስረዱት ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ በቀጠናው የታዩ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ቁጥር ከ63 ከመቶ በላይ ጨምሯል።
በሽታዎቹን የሚያመጡ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የገለፁት ኦቲም፣ ኢቦላ ለምሳሌ በሰው ልጆች ምክንያት እንደሚባባስ ያስረዳሉ። የህዝብ ብዛት እየጨመረ ሲሄድ እና ሰዎች የዱር አራዊት መኖሪያ አካባቢዎችን ጥሰው ሲገቡ በሰው እና በእንስሳት መካከል የሚኖረው ንክኪ የሚጨምር በመሆኑ በሽታው ወደ ሰዎች እንዲዛመት ያደርጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የሙቀት መጠን መጨመር እና የአየር ንብረት ለውጦች የኢቦላ ተሸካሚ ቫይረሶችን እንቅስቃሴ እና ዝውውር እንደሚያባብስም ኦቲም ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢቦላ በኡጋንዳ ከተነሳበት የሙቤንዴ አውራጃ ተስፋፍቶ በሰባት ወረዳዎች ውስጥ የተዛመተ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀ ሲሆን እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 131 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 48ቱ ህይወታቸው አልፏል።