በሄይቲ ዋና ከተማዋ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ ውስጥ በስፋት በሚታወቅ ጋዜጠኛ ላይ ትናንት የግድያ ሙከራ ተካሂዷል።
ሮበርሰን አልፋንዝ የተባለው ጋዜጠኛ ወደ ሥራ በማምራት ላይ ሳለ መኪናው በጥይት ተበሳስቷል።
ለ ኑቨሊስት ለተባለ ዕለታዊ ጋዜጣና ማጊክ-9 ለተባለ ሬዲዮ ጣቢያ የሚሠራው አልፋንዝ ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን ይተርፋል ተብሎ ይጠበቃል። እስከ አሁን ሁለት ቀዶ ጥገና ተካሂዶለታል።
በሌላ በኩል ለቀናት ጠፍቶ የነበረ የሌላ ጋዜጠኛ አስከሬን ትናንት ማግኘታቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
እስከአሁን በሁለቱም ጉዳይ ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው የለም። ባለፈው ዓመት ፕሬዝደንት ዦቨነል ሞይስ በነፍሰ ገዳዮች ከተገደሉ በኋላ ጉልበት ያገኙት ታፋላሚ ወሮበሎች ጋዜጠኞችን ኢላማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በሜክሲኮ የሚገኙ ሴት ጋዜጠኞች ደግሞ አደጋ እየተጋረጠባቸው ቢሆንም ሥራቸውን ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
በተለይም ሴቶችን ኢላማ ያደረገ የቃላት ስድብና የሳይበር ትንኮሳ እየጨመረ በመምጣት ላይ ነው ተብሏል።
የቪኦኤው ቪሴንቴ ካልደሮን ከሜክሲኮ እንደዘገበው ጋዜጠኞቹ “ጥቃቱ ከሥራቸን አይገታንም” ብለዋል።
የመንግስት ሙስናንና የአደንዛዥ ዕጽ አስተላላፊዎችን በማጋለጣቸው ትንኮሳ እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ታውቋል።
አርቲክል 19 የተሰኘው የሰብዓዊ መብትን እና ነጻ ሃሳብን የሚያበረታታ ቡድን እንዳለው፣ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወሮች ውስጥ ብቻ በጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ የቃላት፣ አካላዊ፣ እና በኢንተርኔት የሚደረግ ጥቃት በሜክሲኮ በ51 በመቶ ጨምሯል።
አብዛኞቹ ዛቻዎች የሚመጡትም ከመንግስት ባለሥልጣናት ሲሆን፣ ሴቶች ደግሞ ዋና ኢላማ መሆናቸው ታውቋል።