ትናንት ስልጣን የተረከቡት አዲሱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ዛሬ ለመጀመሪያ ግዜ ከፓርላማ ከተቃዋሚዎቻቸውን አግኝተው መንግስታቸው ኢኮኖሚውን እንደሚያረጋጋና ቀጣይነትን እንደሚያረጋግጥ ቃል ገብተዋል። የስድስት ሳምንቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ የታክስ እቅድ ገበያውን ካወከው በኋላ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈርጀ ብዙ የሆነውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቅረፍ ቃል ገብተዋል።
የመንግስትን ቀጣይነት ለማሳየት ይመስላል ከቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊዝ ትረስ እና ቦሪስ ጆንሶን የካቢኔ አባላት ውስጥ ልምድ ያላቸውን በአዲሱ ካቢኔያቸው ውስጥ ቀላቅለዋል።
እንደ አሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ ከሆነ ቁልፍ የሆነ የኢኮኖሚ ዕቅዳቸውን ይፋ ማድረጉን ለሶስት ሳምንት አዘግይተውታል። ይህም የተሻለና ትክክለኛ ቅድመ ትንበያ ለማድረግና መንግስት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ መላ እንዲዘይድ ግዜ እንዲኖረው ነው ተብሏል።
“የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር ከባድና አስቸጋሪ ውሳኔ መወሰን አለብን፤ ይህንንም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ነው የምናደርገው። ይበልጥ ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ሁሌም እታደጋለሁ። በኮቪድ ወቅት ያንን አድርገናል፣ አሁንም ያንን እናደርጋለን” ብለዋል ሱናክ ለፓርላማው ሲናገሩ።
በተቃዋሚ ወገን ያሉት ፖለቲከኞች የሱናክ መንግስት ካለፈው በወረሰው ችግር ላይ አተኩረዋል። አሁን እንደገና በተካተትቱትና፣ በቅሌት ምክንያት ስልጣን በለቀቁት የቀድሞ የቦሪስ ጆንሰን የካቢኔ አባላትና፣ የሰባት ሣምንታት ብቻ የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥልጣን ዘመን በነበራችው ሊዝ ትረስ ላይ።