በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቡርኪና ፋሶ አክራሪዎች ወታደሮችንና ሲቪሎችን ገደሉ


 የቡርኪና ፋሶ መፈንቅለ መንግስት መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ (ፎቶ ከፋይል)
የቡርኪና ፋሶ መፈንቅለ መንግስት መሪ ኢብራሂም ትራኦሬ (ፎቶ ከፋይል)

በቡርኪና ፋሶ ሰሜናዊ ክፍል እስላማዊ አክራሪዎች በደፈጣ ባደረሱት ጥቃት ሶስት ወታደሮችንና ስምንት ሲቪል ረዳቶቻቻውን መግደላቸውን የጸጥታ ምንጮች ለኤ.ኤፍ. ፒ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

ወታደሮቹና ረዳት ሲቪሎቹ ቡሩም በተባለ አውራጃ ድንገት በተፈጸመ የደፈጣ ጥቃት እንደተገደሉ አንድ የፀጥታ ምንጭ ተናግረዋል። ሌላ ምንጭ ደግሞ ጥቃት መፈፀሙን አረጋግጠው፣ የሟቾቹ ቁጥር ግን ከዚህ ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በ1950ዎቹ ከፈረንሳይ አገዛዝ ነጻነቷን የተቀዳጀችውና በዓለም ካሉ እጅግ ደሃ ሀገሮች መካከል የምትመደበው ቡርኪና ፋሶ በርካታ መፈንቅለ መንግስቶችን አስተናግዳለች። ከሁለት ሳምንት በፊት በ34 ዓመቱ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ የሚመራ ቡድን ሌቴና ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባን ከስልጣን አባሯል። ዳሚባ ራሳቸው ስልጣኑን የያዙት ባለፈው ጥር ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት ነበር።

በቅርቡ የተካሄዱት መፈንቅለ መንግስቶች የሚካሄዱት ከሰባት ዓመት በፊት ከማሊ ተነስተው የመጡ የእስልምና አክራሪዎችን በተመለከተ በቂ ሥራ አልተሠራም በሚል በሠራዊቱ መካከል መግባባት ባለመኖሩ ነው ተብሏል።

እንደ ዳሚባ ሁሉ፣ ትራኦሬም ከ20 ወራት በኋላ ሃገሪቱን ለሲቪል አስተዳደር ለማስረከብ ቃል ገብተዋል።

XS
SM
MD
LG