በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ አንድ የዕርዳታ ድርጅት ሠራተኛዬ ተገድሏል አለ


ኢንተርናሽናል ረስኪው ኮሚቴ (International Rescue Committee) በመባል የሚታወቅ የሰብዓዊ ድርጅት በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አንድ ሠራተኛው እንደተገደለበት ትናንት ቅዳሜ አስታውቋል።

ድርጅቱ እንዳለው በሽሬ ከተማ ዓርብ ዕለት በደረሰ ፍንዳታ ሕይወት አድን ሰብዓዊ ሥራን በማከናወንና ሴቶችና ሕጻናትን በመርዳት ላይ የነበሩ አባላቸው ተገድለዋል።

እንደ አሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ ከሆነ፣ አንድ ሌላ የድርጅቱ የዕርዳታ ሠራተኛ በፍንዳታው ጉዳት ደርሶበታል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለአሶስዬትድ ፕረስ በላከው ዘገባ በበኩሉ እንዳለው አጋራቸው የሆነው ኢንተርናሽናል ረስኪው ኮሚቴ ሃይል ሰጪ ምግብ፣ በተለይም ለእናቶችና ሕጻናት በሚያከፋፍልበት አካባቢ ፍንዳታ እንደነበር ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል።

“የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብዓዊ ተግባራት ሆን ተብሎ ኢላማ መደረጋቸውን ያወግዛል። በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋት መሠረት ሁሉም ወገኖች የሰብዓዊ ሥራዎችን እና ሠራተኞቻቸውን እንዲያከብሩ እና እንዲጠብቁ ጥሪ እናደርጋለን” ብሏል በመግለጫው።

ኢንተርናሽናል ረስኪው ኮሚቴ ሠራተኛ ሲገደልበት ይህ ሁለተኛው መሆኑ ነው።

በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ በህጻጽ ስደተኞች ጣቢያ አንድ ሠራተኛውን አጥቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በትግራይ እየተባባሰ ያለው ጦርነት እጅግ አሳስቦናል ሲሉ ትናንት በድጋሚ አስታውቀዋል።

ዋና ጸሃፊው በቃል አቀባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ፣ በቅርቡ የጦርነቱ መባባስ ቀድሞውንም አሳሳቢ በነበረው የሰበዓዊ ሁኔታ ላይ ተጨማሪ መከራን አስከትሏል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG