ዳግም ባገረሸው ጦርነት ምክንያት ከሰሜን ወሎ ዞን ቆቦና አካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን ገለጹ።
ዛሬ ከሰዓት ወደ ቀዬአቸው እየተጓዙ መሆናቸውን በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹ አንድ አስተያየት ሰጭ “እየተመለስኩ ያለሁት በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው” ብለዋል፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ ዓለሙ ይመር በሰጡን ማብራሪያ ደግሞ፣ “ተመዝግበው በመጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ” ያሏቸውን “ከ150 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ከነገ ጀምሮ ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ መመለስ የጀመሩት፣ ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከቆየባቸው የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ አካባቢዎች መውጣቱ መነገሩን ተከትሎ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የአየር ኃይሎች በአዲ ዳዕሮ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ዒላማ ያደረገ የድሮን ጥቃት ፈጽመዋል” ሲሉ የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገፃቸው ከሰዋል፡፡
ከኢትዮጵያም ይሁን ከኤርትራ መንግሥት በኩል እስካሁን ለዚህ ክስ የተሰጠ ምላሽም ይሁን መግለጫ የለም፡፡
በተያያዘ ዜና፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳይ ከኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል፡፡