በጥር ወር በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ የተካሄደውን የመንግስት ግልበጣ ተከትሎ ስልጣን የያዘውን ወታደራዊ መንግስት ለመደገፍ ሰልፍ የወጡ ሰዎች የሩሲያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል። አንዳንዶች እንደውም ሀገራቸው ከፈረንሳይ ጋር ያላትን አጋርነት ትታ ፊቷን ወደ ሞስኮ እንድታዞር መንግስታቸውን ጠይቀዋል።
"ፈረንሳይን ከዚህ በኃላ አንፈልግም። እዚህ የመጣነው ሩሲያ እንድትከላከልልን ስለምንፈልግ ነው። ፈረንሳይ እንዲሳካልን ያደረገችው ምንም ነገር የለም"
በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክም እንዲሁ መንግስት ከታጣቂዎች ጋር ለሚያደርገው ውጊያ የሩሲያ ተዋጊዎች ድጋፍ መስጠታቸውን ተከትሎ የራሽያ ኃይሎች አንዲት ሴት እና ልጇን ሲያድኑ የሚያሳይ ሀውልት በዋና ከተማው እንዲቆም አድርገዋል።
እነዚህ ሁኔታዎች ሩሲያ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እያደገ መሄዱን ማሳያ ናቸው። በተለይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባደረገችው ወረራ ምክንያት በምዕራቡ ዓለም የተጣለባትን ማዕቀቦች ተከትሎ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር መሪዎቿ በተደጋጋሚ ወደ አፍሪካ መመላለስ ጀምረዋል።
ይህ ያሳሰባቸው የምዕራቡ ዓለም ሀገራትም እንዲሁ ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ አዲስ ለማጠናከር እየሞከሩ ነው። ለምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ከፍተኛ ባለስልጣኖቿን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እየላከች ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በነሐሴ ወር ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ባደረጉት ጉዞ መንግስታቸው ከአፍሪካ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለማደስ ያወጣውን አዲስ የአፍሪካ ፖሊሲ አስተዋውቀዋል። ፖሊሲው በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን እንደሚያበረታታም ገልፀዋል።
የፖለቲካ ተንታኞች ታዲያ ሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪካ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያደርጉትን ፉክክር ቀዝቃዛው ጦርነት እንደገና ለመቀስቀሱ ምልክት አድርገው የሚመለከቱት ሲሆን አፍሪካ ለሁለቱም ሀገሮች የጥቅም ማራመጃ እንደሆነች ይገልፃሉ። አሜሪካን ሀገር በሚገኘው ሞርጋን ስቴት ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጌታቸው መታፈሪያ -
ካናዳ በሚገኘው ባልሲሊ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ትምህርት ቤት መምህርና በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ በርካታ ጥናቶችን ያካሄዱን ፕሮፌሰርን አን ፊልትዝ ዠራልድም እንዲሁ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሰው ሀይል ሀብት ያላት በመሆኗ በምስራቁም ሆነ ምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ከፍተኛ ተፈላጊ መሆኗን ያሰምሩበታል።
"አፍሪካ በተለይ አሁን ተፈላጊ ወደሆነው አረንጓዴ እና ንፁህ ዓለም ወደፊት ማሻገር የሚችሉ እና ኢኮኖሚው በዋናነት የሚፈልጋቸው የተፈጥሮ ሀብቶች አሏት። ለምሳሌ እንደ ሊቲየም የመሳሰሉ ማዕድኖች እና ውሃ። የስነ-ምድር አጥኚዎች እና የአየር ሁኔታ ተንታኞች ወደፊት ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥም ይናገራሉ። አሁን ምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ድርቅ ውስጥ ቢሆንም አብዛኛው የውሃ ሀብት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ነው የሚገኘው። በተጨማሪም ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከህዝባቸው 70 ከመቶ የሚሆነው ከ30 ዓመት በታች ነው። ይሄ ደግሞ ወደፊት የሚያሻግር የሰው ሀብት እና የሰው ሀይል ነው።"
ፕሮፌሰር ጌታቸው በ20ኛው ክፍለዘመን በሶቪየት ህብረት እና በምዕራቡ አለም መካከል የታየው ቀዝቃዛ ጦርነት በዋናነት በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አሁን የሚታየው ግን መልኩን የቀየረ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በቀደመው ቀዝቃዛው ጦርነት ይታዩ የነበሩ የርዕዮተ ዓለም አመለካከት ልዩነቶች አሁንም መቀጠላቸውን የሚያሰምሩበት ፊትዝ ዠራልድ በበኩላቸው እንዳዲስ ያገረሸው ቀዝቃዛ ጦርነት ግን በዋናነት በኢኮኖሚ ጥቃም ላይ የተመሰረተ ነው ይላሉ።
" አዲሱ ቀዝቃዛ ጦነት የኢክኖሚ ጦርነት ነው፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለማግኘት የሚደረግ ሩጫ። አብዛኞቹ የምዕራብ ሀገራት ወደ ንፁህና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመሻገር የሚያደርጉት ጥረት በተለይ የፖለቲካ ስልጣንን ከማስጠበቅ አንፃር በርካታ ችግሮችን እና መከፋፈሎችን ፈጥሯል። መካከለኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የኢኮኖሚ አጀንዳ ለማስጠበቅ ለሚደረገው ጥረት ደግሞ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መሸጋገርን ግድ ይላል። ያ በአፍሪካ ላይ ተፅእኖ አለው።"
በዚህ በአዲሱ የቀዝቃዛ ጦርነት አፍሪካን መፋለሚያ መድረክ ያደረጓት በቀድሞ ሶቪየት ህብረት ፈርጣማ ክንድ የነበራት ሩሲያ እና አሜሪካ ብቻ አይደሉም። ቻይና፣ ህንድ ጃፓን እና ብራዚልን የመሳሰሉ ሀገራትም እንዲሁ ከአፍሪካ ጋር የነበራቸውን የቀደመ ግንኙነት ለማጥበቅ ወይም እንደአዲስ ለመመስረት የሚጥሩ ሀገራት ናቸው።
በአፍሪካ ቀንድ ላለፉት 40 አመታት ያልታየ ድርቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን የረሃብ አደጋ ላይ ጥሏል። የሩሲያ እና የአሜሪካ ባለስልጣናት በቅርቡ ወደ አካባቢው ባደረጉት ተደጋጋሚ ጉዞ ደግሞ ለተከሰተው የምግብ እጥረት እርስ በእርስ ተወነጃጅለዋል። የነዚህ ሀገራት አይን በአካባቢው ማንዣበብ በተለይ በድርቅ እና በተለያዩ ቀውሶች ለተጠቁት ሀገራት ምን ትርጉም አለው? ለሚለው ጥያቄ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሲመልሱ
በእነደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እና የስራቴጂክ አቀማመጥ ወይም ጂኦፖለቲክስ ፉክክር ውስጥ አጣብቂኝ የገቡት የአፍሪካ ሀገራት ምን ማድረግ ይችላሉ ለሚለው ጥያቄ ፕሮፌሰር ፊትዝዤራልድ መፍትሄው በአፍሪካውያን እጅ መሆኑን ይገልፃሉ።
"የተማረ ህብረተሰብ የራሱን የተፈጥሮ ሀብት የመቆጣጠር አቅም ይኖረዋል። የራስን የተፈጥሮ ሀብት መምራት ካልተቻለ፣ በር ላይ እነዚህን ሀብቶች ሊቆጣጠሩ የሚፈልጉ በርካታ ተጫዋቾች ተሰልፈው ቆመዋል። በተለይ ደግሞ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀጉ ሀገራት ከሆኑ። ስለዚህ ለአፍሪካ ሀገራት መረጋጋት እና የተማረ ማህበረሰብ መኖር ትልቁና ዋናው ቁልፍ ነገር ነው። ያሉትን ሀብቶች በሚፈልገው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል የሚችል እውቀት እና ብቃትም እጅግ አስፈላጊ ነው። ይሄ የሚያመለክተው ትምህርት ምን ያክል አስፈላጊ መሆኑን ነው። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ መረጃ ለአንድ ሀገር እንደ ሀይል ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። ግን እነዚህ ሁሉ ያለጥሩ ፖሊሲዎች፣ ያለ ጥሩ ስትራቴጂዎች እና በወረቀት ያለውን ወደተግባር መለወጥ የሚችል አቅም ትርጉም የላቸውም።"
በዚህ የሚስማሙት ፕሮፌሰር ጌታቸውም አፍሪካ ሳትወድ ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት ጠንካራ አመራር ሊኖራት እንደሚገባ አስምረውበታል።
የቀድሞ ቀዝቃዛ ጦርነት ከአመታት ፍልሚያ በኃላ በምዕራብ ሀገራት የበላይነት ተጠናቋል። በርካታ ሀገራት ተዋናይ የሆኑበት አዲሱ ቀዝቃዛ ጦርነት ደግሞ በማን ድል አድራጊነት እንደሚጠናቀቅ ወይም ምን አይነት ታሪካዊ ክስተቶችን ጥሎ እንደሚያልፍ በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።